በድሬዳዋ የኮሪደር ልማት ለመጀመር የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ተገለፀ

በድሬዳዋ የከተማ ኮሪደር ልማት ለመጀመር የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ አስታወቁ።

ጥናቱን በዋናነት የሚያከናውኑት የድሬዳዋ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮና የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ሲሆኑ፤ ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት የጥናት ቡድኑ አባላት እንዲሆኑ ተደርጓል።

የጥናት ቡድኑ አባላት በሚቀጥሉት አራት ወራት በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ዛሬ ከአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንደተናገሩት፤ ጥናቱ ሲጠናቀቅ የኮሪደር ልማቱ በመጪው በጀት ዓመት በሁለት አቅጣጫ ተከፍሎ በከተማዋ ዋና ዋና ኮሪደሮች ግራና ቀኝ የሚተገበር ይሆናል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ

የጥናቱ ቡድን የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመቀመር ሌት ተቀን በመረባረብ ጥናቱን በጥራት ማጠናቀቅ እንዳለበት አመልክተው፤ “በከተማ ኮሪደር ልማቱ ሳቢያ የሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማስፈር ከወዲሁ ዝግጅት ይደረጋል” ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ለአዳዲስ ልማቶች እያሳየ የሚገኘው ፍላጎትና ትብብር ለጥናት ቡድኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለፃ፤ በድሬዳዋ በመጪው በጀት ዓመት የሚተገበረው የከተማ ኮሪደር ልማት ድሬዳዋን ውብና ምቹ የመኖሪያ፤ የስራና የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ የብልጽግና ጉዞውን ለማሳካት ያግዛል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳጅድ አልይ በበኩላቸው፤ “ጥናቱ በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ በማሳተፍ የሚከናወን ይሆናል” ብለዋል።

ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲለወጥ ድሬዳዋ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ከተማ በማድረግ የነዋሪውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመመለስ ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ የኮሪደር ልማት የጥናት ቡድን አባላት

በዋና ዋና የከተማዋ ኮሪደሮች ላይ የሚካሄደው የከተማ ኮሪደር ልማት የህዝብን የማህበራዊና የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ተግዳሮት የሚፈታ ይሆናል ያሉት ደግሞ ከድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የጥናት ቡድን አባል አቶ ወንድወሰን ጀንበሬ ናቸው።

እርሳቸው እንዳሉት በተለይ በአሁን ወቅት በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በማስቀረት ልማትን ያሳልጣል።

የከተማ ኮሪደር ልማቱ ከሳብያን ቻይና ድልድይ እስከ ሐረር መውጫ፤ ከከንቲባ ፅህፈት ቤት እስከ ሰባተኛ አስፓልት ያሉትን ኮሪደሮች የሚሸፍናቸው መዳረሻዎች ናቸው።

በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ በኮኔል – ታይዋን – ገንደ ገራዳ አስፋልት መጨረሻ፣ ከለገሃር አደባባይ እስከ ለገሃሬ አስፋልት እና ከድሬዳዋ አየር ማረፊያ እስከ ምድር ባቡር የሚሸፈን መሆኑ ታውቋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share to your Network:

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *