የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከዩኤን ሃቢታት (UN-Habitat) ዋና ዳይሬክተር አናክላውዲያ ሮስባክ ጋር በአዲስ አበባ የከተማ ለውጥና ዘላቂ ልማት ዙሪያ ያለውን ትብብር ለማጠናከር መወያየታቸውን ገለጹ።
ከተማችን በሻንጋይ በተካሄደው የዓለም የከተሞች ቀን ያገኘችውን የዘላቂ የከተሞች ልማት ሽልማትና በሴኡል የተሰጣትን የስማርት ከተማ ዕውቅና በማስመልከት፣ የዩኤን ሃቢታት ዋና ዳይሬክተር እንኳን ደስ አላችሁ ማለታቸውን ገልጸው፣ እኛም ምስጋናችንን ገልጸናል ብለዋል።
በቀጣይም በከተማ ልማትና ፕላን ያለንን ትብብር በማጠናከር፣ ቀጣዩን የዓለም የከተሞች ቀን በአዲስ አበባ በስኬት ለማክበር በቅንጅት ለመሥራት መስማማታቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ጠቅሰዋል።
በቅርቡ የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባር ለማሸጋገርም የጋራ የትግበራና የክትትል ሥርዓት በመዘርጋት፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ፕሮጀክቶች በመለየት ላይ መወያየታቸውን አመላክተዋል።
አዲስ አበባ COP32ን ለማስተናገድ በምትዘጋጅበት ወቅት፣ የUN-Habitat ስትራቴጂያዊና ቴክኒካዊ አጋርነት የከተማችንን የልማት አጀንዳ ለማፋጠንና ዘላቂ ውጤት ለማስገኘት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ነው ያሉት።
ዓላማችን አጋርነትን ወደ ተግባር፣ ተግባርን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር ለሕዝባችን ዘላቂ ጥቅም ማስገኘት ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን


















