በአገሪቱ የሚታየውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት ዜጎች ከገቢያቸው ላይ እየከፈሉ በረዥም ጊዜ ሂደት የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አሰራር መዘርጋቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቤት ልማት እቅዶችን ለማሳካት ዘላቂና ህጋዊ ማዕቀፍና አዲስ ፖሊሲ ተቀርጾ በካቤኒ ጸድቋልም ብለዋል።
በዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ለሚኖሩ ዜጎች የሚመጥኑ የቤት አቅርቦት አማራጮችን በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚገባና ባንኮችን ጨምሮ የፋይናንስ ተቋማት በቤት ልማት ዘርፍ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባው የምክር ቤት አባላት በጥያቄያቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና የ2019 በጀት ላይ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ ቤት መግዛት የሚቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በረዥም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ዜጎች በኪራይ ጀምረው በሂደት የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አሰራርም ይተገበራል።
መንግስት የቤት ልማት እቅዶችን ለማሳካት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው ያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰራሩን ዘላቂና ህጋዊ ማዕቀፍ ለመስጠት አዲስ ፖሊሲ ተቀርጾ በካቤኒ ጸድቋል ብለዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቤቶች መገንባታቸውን በመጥቀስ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት መታቀዱን ተናግረዋል።
የዜጎችን የመግዛት አቅም ያማከለ የመኖሪያ ቤት ግንባታ አማራጭን ማስፋት እንደሚገባ ገልፀው ግንባታው በመንግስት ብቻ ሳይሆን በግል ዘርፍ፣ በመንግስትና በግል አጋርነትና በሌሎች አማራጮች ይከናወናል።
የቤት ግንባታዎችን እውን ለማድረግ የኮንስትራክሽን ፋብሪካዎች ግብዓቶችን እያመረቱ ነው፣ ሲሚንቶ፣ ብረትና ሴራሚክስን የመሳሰሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት ተግባራትም እየተከናወነ ይገኛል።
ምንጭ: ጋዜጣ_ፕላ


















