በሀገራችን የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ከሚከናወንባቸው ህጋዊ መንገዶች አንዱ በአክሲዮን ማልማት ነው።
ይህ የአክሲዮን የሪል እስቴት ኢንቨስትመት በሀገራችን አዋጭ ነው ወይ ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ የሚያደርጉት ሁኔታዎች ይታያሉ ለዚህ ዋናው ምክንያቱ ጥቂት የማይባሉ በመዲናችንና በአንዳድንድ በክልል ከተሞች በአክሲዮን የተደራጁ አልሚዎች ከፕሮጀክቱ ልማት ይልቅ በየጊዜው እያደገ የሚመጣው የአክሲዮን ዋጋ ሽያጭ ነው። ይህ ገንዘብን ዋጋ ከመስጠት አንጻር ትክክለኛ ቢመስልም የሪል እስቴት ልማትን ስኬትን አደጋ ላይ እየከተተ እየመጣ ነው።
ጥቂት የማይባሉ በአክሲዮን የተመሰረቱ የሪል እስቴት አልሚ ተቋማት መስራቾቹን ጨምሮ በርካቶች አክሲዮኖቻቸውን ሸጠው ወጥተው በሌሎች ሲተዳደሩ የገዙት ደግሞ እንደገና ሲሸጡ…ይሄንን ያክል የቆጠበ… መሬት የገዛ … ይሄንን ያክል የሱቅ ዕጣ …ያንን ያክል የመኖሪያቤት ዕጣ ….እያሉ ማስታወቂያ የሚያሰሩ በርካቶች ናቸው።
ብዙዎች ከአስር ዓመታት በላይ ቆጥበው ውጤት ያላሳዩ ፣ ከበርካታ ዓመታት ቆይታ በኋላ አብሮ የሚያለማ ባለሀብት የሚያፈላልጉ ፣ በጊዜ መራዘም ምክንያት ጅምር ፕሮጀክቶቻቸው አዋጭነታቸውንና ተፈላጊነታቸውን እያጡ የመጡ፣ የመጀመሪያዎቹን ወለሎች ሰጥቶ አየሩን የሚወስድ የሚፈልጉ ….በርካታ ናቸው።
ቆም ብሎ ላሰበው በመርካቶ የንግድ ተቋማት ግንባታ ተጀምሮ በተለያዩ የመዲናችን ክፍሎች ስኬትን ያሳየን ብዙዎችን ውጤታማ ያደረገው የአክሲዮን የሪል እስቴት ግንባታ አሁን ቆሌው የተገፈፈና መስመሩን እየሳተ የመጣ ይመስላል።
የወቅቱም ሁኔታም ተጨምሮበት የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ስራ ብዙ ገንዘብ ማሰባሰብ ብቻ የሚሰራ ወይም ስኬታማ የሚሆን አይደለም።
ከገንዘብ ባሻገር በአክሲዮን የሚደረጉ የሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ስራዎች የሚከተሉትን ታሳቢ ቢያደርጉ ይጠቀማሉ:-
፩) የገበያ ፍላጎት መጠናት አለበት ይህም ኢንቨስትመንቱ ከመጀመሩ በፊት፣ ከግንባታ በፊት፣ በግንባታ ሂደት ወቅት፣ ከሽያጭ በፊት …በተለያዩ ወቅቶች እየተጠና እየተከለሰ መሄድ አለበት
፪) ኢንቨስትመንቱና ፕሮጀክትማኔጅመንቱ እውቀት በዘለቃቸው የልማት ቡድን (Development Team ) መመራት አለበት
፫) የሃገራችንን የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ሁኔታ ያገናዘበና መጻኢውን ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባዋል
፬) በየወቅቱ የሚወጡ የመንግስት መመሪያዎችና ፖሊሲዎችን መረዳትን ይጠይቃል።
በአክሲዮን ከተደራጁ አልሚዎች ቤት ወይም አክሲዮን የሚገዙ የሚከተሉትን ታሳቢ ቢያደርጉ ያተርፋሉ:-
፩)ብሊገዙት ባሰቡት የቤት ወይም አክሲዮን ግብይት ውስጥ ያለውን ወቅታዊ የግብይት ሁኔታዎችን ማጥናት
፪) የአልሚዎቹ ወቅታዊ የገንዘብ አቅምን ለማወቅ መሞከር
፫) የአክሲዮኑ ያለፈው የስኬት ሂደትን መገምገም። ለምሳሌ በአክሲዮን ሽያጭና ዝውውር ላይ ያተኩራሉ ወይስ ግንባታው ላይ? ሰዎችስ ስለ አልሚዎቹ ምን ያ
ይላሉ?
፬) የሚሰጡት መረጃዎች ግልጽነትን መገምገም።
፭) ገበያ ውስጥ ያላቸው ተፈላጊነት ስምና ዝናቸውን ማጥናት
፮) ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት የፋይናንስና የሪል እስቴት ግብይትና ኢንቨስትመንት ባለሙያዎችን ያማክሩ።
በደምሳሳው የአክሲዮን ኢንቨስትመንት ያውም በሪል እስቴት ከፍተኛ ጥንቄቄ የሚፈልግና በተደራጀ መረጃ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መወሰን የሚፈልግ ተግባር ነው።
እየተጠነቀቅነ በእውቀት እንገበያይ።


















