በዛሬው ዕለት የተፈረመው የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስ ስምምነት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለታቀደው የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች ግንባታ ስኬት ወሳኝ ነው አሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፡፡
በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችለው ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት መፈረሙ ይታወቃል፡፡
አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ስምምነቱን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን መካከል የተደረገው የቤት መግዣ ብድር (ሞርጌጅ) ፋይናንስ ስምምነት የኢትዮጵያን የቤት አቅርቦት ታሪክ የሚቀይር ነው ብለዋል፡፡
በተለይም የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስ ስምምነቱ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለታቀደው የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች ግንባታ ስኬት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት እውን ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምንጭ:-ኤፍ ኤም ሲ

















