በኢትዮጵያ የነዋሪዎችን የቤት ተደራሽነት ለማሟላት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ አዋጅ ቁጥር 370/1995 በጋራ ሕንፃ ቤት ባለቤትነት መሠረት ተደንግጎ በተጀመረው የኮንዶሚኒየም ቤት ቁጠባ ፕሮግራም፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ተመዝግበው የቤት ቁጠባ እንደጀመሩ፣ ዛሬም ድረስ እየቆጠቡ እንዳሉና ዕጣ ደርሷቸው የቤት ባለቤት የሆኑ እንዳሉም ይታወቃል፡፡
በ1997 ዓ.ም. እና 2005 ዓ.ም. የኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት ለዓመታት መሥፈርቱን አሟልተው በመመዝገብ ሲቆጥቡ የነበሩ ቆጣቢዎች ቤት የማግኘታቸው ነገር የውኃ ሽታ እንደሆነባቸውም ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡
በ1997 ዓ.ም. የ20/80 የኮንዶሚኒየም ባለ አንድ መኝታ ቤት ቁጠባ ተመዝጋቢ ሲሆኑ፣ ለ21 ዓመታት ያህል ያለማቋረጥ እንደቆጠቡ፣ ነገር ግን አሁንም የቤት ዕጣ እንዳልደረሳቸው አንድ ተመዝጋቢ ነግረውናል፡፡
አክለውም ‹‹በቤት ኪራይ ለዓመታት ተንከራትቻለሁ፣ ቤት በማግኘት ተስፋ ያለመሰልቸት ብቆጥብም ከእኔ በኋላ የተመዘገቡ ሲደርሳቸው ታዝቤያለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ከየትም አምጥቼ በቆጠብኩት ገንዘብ መንግሥት ቤቴን እንዲያስረክበኝ ስል እጠይቃለሁ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችን ተመዝጋቢ፣ የ2005 የ40/60 ኮንዶሚኒየም ቤት ቆጣቢ ስትሆን፣ ለ13 ዓመታት ያህል ቆጥባ ዕጣው እንዳልደረሳት ተናግራለች፡፡ የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ይህች ሴት፣ ‹‹የቤት ዕጣው ደርሶኝ ቢሆን ኖሮ ለቤት ኪራይ የማወጣውን ወጪ ልጆቼን ጥሩ ቦታ አስተምርበት ነበር፤›› ስትል ምሬቷን ትገልጻለች፡፡
ይህን ጉዳይ በተመለከተ በ2005፣ 20/80 እና 40/60 የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ኮሚቴ የሆነችው ወ/ሮ ሔለን ኤፍሬም ከሪፖርተር ጋር በነበራት ቆይታ እንደገለጸችው፣ በምትሠራበት ኮሚቴ ውስጥ በማኅበራዊ ድረ ገጽ የተመዘገቡ ከአራት ሺሕ በላይ ቤት ተመዝጋቢዎች አሉ፡፡ በተደጋጋሚም ጥያቄያቸውን ይዘው የከተማ አስተዳደር፣ የቤቶች ልማት ቢሮና የቤቶች ልማት ኮርፖሬሸን ተመላልሰዋል፡፡
ነገር ግን ‹ሳትሰለቹ ቆጥቡ› ከሚል ተስፋ የተለየ በተጨባጭ የሰጧቸው መፍትሔ እንደሌለ ገልጻለች፡፡ ‹‹መንግሥት የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለልማት ተነሺዎች እየሰጠ ለዓመታት የቆጠብነውን ነዋሪዎች የማይሰጥበትን ምክንያት ይግለጽልን፤›› ስትልም ጠይቃለች፡፡
የሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲሄዱም ‹ሌሎች የቤት አማራጮች አሉን ብራችሁን ከፍ አድርጋችሁ ቆጥቡ፤› እንደሚባሉ ጭምር ገልጻለች፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን የኮንዶሚኒየም ቤት ቁጠባ ፕሮግራም የመጣበት ዓላማ ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ላይ የሚገኘውን ነዋሪዎች ለማገዝ በመሆኑ፣ ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ ድምፃቸውን እንደሚያሰሙ አክላለች፡፡
ወ/ሮ ሔለን፣ ከዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱ ጋርም በተያያዘም ፍትሐዊነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላትም ገልጻለች፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጵያ ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ሰርቪስ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ አጥናፌ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት የቆጠቡ ተመዝጋቢዎች የ20/80 510 ሺሕ የ40/60 ተመዝጋቢዎች 90 ሺሕ በድምሩ 600 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ሲሆኑ፣ ከነዚህም ውስጥ ለ370 ሺሕ ተመዝጋቢዎች ቤት እንዳስረከቡ ተናግረዋል፡፡
ለቀሪዎቹ ተመዝጋቢዎችና ቆጣቢዎች ቤት ያላስረከቡትን አስመልክቶ ላቀረብነው ጥያቄ፣ ኮንዶሚኒየም ቤቱን በጊዜው ያላስረከቡበት አጋጥሟቸው በነበረ የብድር ጫና እንደሆነና ባለፉት አምስት ዓመታት መሥሪያ ቤታቸው 40 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ዕዳ እንደከፈለ ገልጸዋል፡፡
ቀሪ 30 ቢሊዮን ብር ብድር እንደሚቀር፣ መንግሥት ከ2011 እስከ 2018 ዓ.ም. ለቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን 50 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ እንደደጎመ፣ ባለፉት አምስት ዓመታትም 139 ሺሕ የሚሆኑ ያልተጠናቀቁ ቤቶችን አጠናቀው እንዳስረከቡ አክለዋል፡፡
አሁን ላይ ቤቶቹን አጠናቆ ለማስረከብ አበዳሪ ተቋማትን እየጠበቁ እንዳለና ብድሩ በተገኘ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቶቹን እንደሚያስረክቡ፣ መንግሥት የቤት ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር ያስገነባቸውን ቤቶች በሚመርቅበት ወቅት የሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በኢትዮጵያ ሲተገበር የነበረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግብር ከታለመለት ዓላማ አንፃር ስህተት እንደነበር ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ: Ethiopian Reporter


















