ሀገር በቀሉ የጃምቦ ሪል እስቴት እህት ኩባንያ ጃምቦ ኮንስትራክሽን፣ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ቡርኪናፋሶ በቤት ልማት ዘርፍ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ታሪካዊ ስምምነት ከሀገሪቱ ብሔራዊ የከተማ መሬት ልማት ኮርፖሬሽን (SONATUR) ጋር በአዲስ አበባ ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የጃምቦ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ሰይፉ እና የSONATUR ዋና ዳይሬክተር ቡሬማ ኡዋታራ የተፈራረሙት ሲሆን፣ ይህም ጃምቦ በኢትዮጵያ ያካበተውን ሰፊ የሪል እስቴት ልምድ ወደ ሌላ የአፍሪካ ሀገር በማስፋፋት “አፍሪካ ለአፍሪካ” የሚለውን መርህ በተግባር ያሳየበት ትልቅ እርምጃ ሆኗል።
ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ በርካታ ስኬታማ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን ያከናወነው ጃምቦ ኮንስትራክሽን፣ በደቡብ ሱዳንና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የጀመረውን አህጉራዊ ተሳትፎ አሁን ላይ ወደ ቡርኪናፋሶ አሳድጓል።
ይህ ታሪካዊ ስምምነት የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ ኩባንያዎች በውጭ ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት የሚያጎለብት ከመሆኑም በላይ፣ የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዕድገትና የቴክኖሎጂ አቅም በአህጉራዊ መድረክ ላይ በጉልህ የሚያሳይ አዲስ ምዕራፍ ነው ተብሏል።
ምንጭ: addisadmassnews


















