የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ በከተማዋ ከ10 ወለል በላይ በሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የነበረውን የአሳንሰር (ሊፍት) ችግር ለመፍታት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታወቀ።
የቢሮው ሃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ በከተማዋ ምክር ቤት 5ኛ አመት የ10ኛ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንደገለጹት፣ እነዚህ ቤቶች በግንባታ ወቅት የአሳንሰር እቅድ እንዳልነበራቸው አስታውሰዋል።
ከጥቂት አመታት በፊት እቅድ ተይዞላቸው ወደ ጨረታ ቢገቡም፣ በጨረታው ሂደት በተከሰቱ የተለያዩ ችግሮች ስራው ተስተጓጉሎ እንደነበርም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን ስራው ተጀምሮ አንዳንድ የመኖሪያ ሳይቶች ሊፍቶቹን በመግጠም አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የቢሮው ሃላፊ ተናግረዋል። ለስራው ቅድሚያ የተሰጠው ጂ ፕላስ 15 (G+15) ለሆኑ ህንጻዎች ነው።
በአረብሳ አካባቢ በሚገኘው የ20/80 መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ላይ ሊፍት መገጠሚያነት የሚያስፈልገው የሲቪል ወርክ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና የሊፍት እቃዎቹ ቀድመው የተዘጋጁ በመሆናቸው፣ የሲቪል ስራው እንደተጠናቀቀ የመግጠም ስራው እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ወ/ሮ ቅድስት አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ባሉ አዳዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ እንደዚህ አይነት የአሳንሰር ችግሮች እንደማይፈጠሩ አረጋግጠዋል።
ምንጭ: ethiofm


















