አብዛኛውን የከተማውን ክፍል የሸፈነው የኮሪደር ልማት ከተካሄደ በኋላ፣ አዲስ አበባ ለታላላቅ ከበርቴዎች የሚሆኑ ግንባር ቦታዎችን ማምረት ጀምራለች።
እነዚህ ቦታዎች በዋዛ አይገኙም። የተጠና ፕሮጀክት ያዘጋጀና አስተማማኝ የገቢ አቅም ያለው አልሚ መሆን ይጠበቅበታል።
ይህ የቦታ ጥያቄ ለከተማው አስተዳደር ሲቀርብ፣ ካቢኔው አጥንቶ ከመረመረው በኋላ ይሁንታ ከሰጠ፣ ጉዳዩ በቀጥታ ከፒያሳ ፣ ለም ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ይወርዳል።
አልሚውም በምደባ ሁነኛ ቦታ የማግኘት ዕድል ይኖረዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ አልሚዎች በዚህ አሠራር ግንባርና ኪስ ቦታዎችን ተረክበዋል።
የቦታ ተረካቢ ባለሀብቶች ሁሉ ግን ወደ ልማት ገብተዋል ማለት አይቻልም። አብዛኞቹ የተለያዩ ምክንያቶችን እያቀረቡ ወደ ግንባታ መግባት አለመቻላቸውን ይገልፃሉ – ለሦስተኛ ወገን የሊዝ መብታቸውን የሚሸጡም ፣ ለመሸጥ ያሰቡም ብዙ ናቸው።
ሹመኛ የማይበረክትለት የመሬት ቢሮም ባለፉት አምስት ዓመታት በምደባም ሆነ በጨረታ ቦታ የወሰዱ አልሚዎችን ደግፏል ማለት አይቻልም – በራሳቸው ችግር መገንባት ያልቻሉ አልሚዎች ላይ ውጤታማ እርምጃ ወስዷል ማለትም አይቻልም።
አሁን ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ፣ አቶ መኮንን ያዒን ከኃላፊነት በማንሳት፣ በምትካቸው አቶ መላኩ ታምሩን ሾሟል።
አቶ መላኩ ከዚህ ቀደም የከተማው ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ የከተማውን የመሬት ቁልፍ እንደተረከቡ፣ በመሬት ቢሮው ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች፣ ሌብነትና የአሠራር ችግሮች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ያለ ግንባታ መሬት አጥረው የያዙ “ከበርቴዎች” ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል። የቢሮው ግምገማ እንደሚያሳየውም፣ በምደባና በጨረታ የተሰጡ በርካታ መሬቶች እስካሁን ድረስ ያለ ልማት ታጥረው ተቀምጠዋል።
በሊዝ ውላቸው መሠረት፣ ወደ ግንባታ ያልገቡ አልሚዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታቸው ተሰርዞ፣ ቦታው ወደ መሬት ባንክ እንደሚገባ ቢሮው አስታውቋል።
አቶ መላኩ ከፀጥታ ዘርፍ ወደ መሬት ዘርፍ መምጣታቸው መንግሥት በሕግ ማስከበር ጉዳይ ኮምጠጥ ማለቱን ያሳያል። ይሁን እንጂ የዚህ ሹመት ስኬት የሚለካው ተጨማሪ መሬት በመስጠት ብቻ ሳይሆን ፣ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን ወደ ልማት በማስገባት፣ ብልሹ አሠራርን በመቀነስና የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ጭምር ይሆናል።
በመሬት ዘርፍ ፣ ሰሞኑን መረር ያሉ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ምልክቶች የታዩ በመሆኑ ፣ የፋይናንስ ችግር የሌለባቸው አፈር ቆረጣ ቢጀምሩ ህልማቸውን ማትረፍ እንደሚችሉ የመሬት ስሪት ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው ።
ምንጭ፦ WZ news


















