የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ውስን የሆነው የመሬት ሀብት ለመንግስትና ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ለልማት የተላለፉ ቦታዎች ላይ የሚደረግ የግንባታ ክትትል ከህግ ማስፈፀም ጋር ሊተሳሰር ይገባል ብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በተለያየ አግባባ የተላለፉ መሬቶችን ያለ ልማት አጥረው የያዙ አልሚዎች የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የቢሮው ኃላፊ አቶ መላኩ ታምሩ በየደረጃው ለሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ኃላፊው ይህን የተናገሩት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በምደባና በጨረታ የተላለፉ መሬቶች በሊዝ ውል መሰረት ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ለማረጋጋጥ ከሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር ባካሄዱበት ግምገማ ወቅት ነው፡፡
በመድረኩ እንደተመላከተው ቢሮው በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ባደረገው ልዩ የግንባታ ክትትል ንቅናቄ በርከታ አልሚዎች ለልማት የተላለፉ ቦታዎችን አጥረው ማስቀመጣቸው ተለይቷል፡፡
አልሚዎቹ የሊዝ ውሉን አክብረው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በየደረጃው የተካሄደ ቢሆንም ዛሬም ወደ ትግበራ ከመግባት ይልቅ አጥጋቢ ያልሆነ ምክንያት በመደርደር የሊዝ ውል እንዲራዘምላቸው እየጠየቁ እንደሆነም በመድረኩ ተነስቷል፡፡
ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች የከተማውን ገፅታ ከማበላሸት ባለፈ የከተማዋ ኢኮኖሚ እንዲቀዛቀዝ አድርጎታል ያሉት የቢሮው ኃላፊው ፤ በቅርቡ በከተማ አስተዳደሩ መሬት አጥረው የያዙ አልሚዎች በአጠረ ቀናት ወደ ተጨባጭ ስራ እንዲገቡ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ እድሉን ተጠቅመው ወደ ልማት በማይገቡ አካላት ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታቸው መክኖ መሬቱ ለሌላ አገልግሎት እንዲውል መመሪያ ሰጥተዋል፡፡


















