ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ሾመዋል።
ላፉት አራት ዓመታት ገደማ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በቦታው ላይ ለዘጠኝ ዓመታት የቆዩትን ዶ/ር ረሻድ ከማልን የሚተኩ ይሆናል።
የኮርፖሬሽኑ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ረሻድ ከማል በበኩላቸው በጨፌ ኦሮሚያ 7ኛ የጨፌ ሥራ ዘመን 1ኛ ዓመት የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ ስድስት ባለስልጣናት አንዱ ሆነዋል።
ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት በመንግሥት የተወረሱ ቤቶችን እንዲያስተዳድር በኤጀንሲ ደረጃ የተቋቋመውን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የመሩት ዶ/ር ረሻድ፣ ተቋሙን ከነበረበት ውስብስብ ችግርና ኪሳራ በማውጣት ትርፋማና ሞዴል የመንግሥት የልማት ድርጅት እንዲሆን አስችለዋል።
በእርሳቸው አመራር ዘመን ኮርፖሬሽኑ ከ41 እጥፍ በላይ የገቢ እድገት ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ ከ28 ዓመታት በላይ ቆሞ የነበረውን የቤት ልማት መርሐ ግብር እንደገና አስጀምሯል።
በተጨማሪም የአሉሚኒየም ፎርምወርክ እና የ3ዲ ኮንክሪት ፕሪንት የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ በሕገወጦችና በሌሎች አካላት ተወስደው የነበሩ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን ይዞታዎች ወደ ተቋሙ እንዲመለሱ አድርጓል።
የዜሮ ኢንቨስትመንት አሠራር ሥልትን በመተግበርም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን በማልማት በርካታ አዳዲስ ሱቆችን ባለቤት መሆን ተችሏል።
በተቋሙ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴርን በሚኒስትርነት በነበሩበት ወቅት የቤት ልማት ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን አድርገዋል።
ለዘርፉ እድገት ማነቆ የነበሩ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ የከተማ ልማት ሥራዎች በሰው ተኮር ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩና የአሠራር ሥርዓቶች እንዲዘመኑ በማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ከዚህ ቀደም ለከተሞች እድገት፣ ለቤት ልማት መስፋፋት እንዲሁም ለዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ አማራጮች ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በቀጣይም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለአገራዊ የቤት ልማት እቅድ ስኬት ያለውን ከፍተኛ ሚና አጠናክረው ያስቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን


















