127 ፕሎቶች የተዘጋጁበት 9ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ ሰነድ ሽያጭ ጥቅምት 30/2019 ዓ.ም ይጀምራል፡፡
ሂደቱም ሙሉ በሙሉ በኦንላይን የሚከናወን ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለዘጠነኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ 127 ፕሎቶችን በስምንት ክፍለ ከተሞች ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የጨረታ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ክብሮም አሰፋ እንደገለፁት፤ ቢሮው የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት 127 ፕሎቶችን በግልፅ የመሬት ሊዝ ጨረታ አወዳድሮ ለማስተላለፍ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሙሉ ለሙሉ አጠናቋል፡፡
ጨረታውን ከብልሹ አሰራር ለማላቀቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሂደቱን መሉ ለሙሉ ዲጅታላይዝ ማድረግ መቻሉን የጠቆሙት አስተባባሪው፤ ከፕላን ተቃርኖና ከይገባኛል ነፃ የሆኑ 127 ፕሎቶች፤ በቦሌ፣ የካ፣ አራዳ፣ ለሚኩራ፣ ጉለሌ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ አቃቂ ቃሊቲ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎቶች በሊዝ ጨረታ አወዳደሮ ለማስተላለፍ ዝግጁ አድርጓል፡፡
የሰነድ ሽያጩም ለዚሁ ዓላማ ተብሎ በተዘጋጀው Website: addislandfarm.gov.et: (https://addislandfarm.gov.et/land-auction) በኦንላይን ከጥቅምት 30/2019 እስከ ህዳር 11/2019 ዓ.ም ባሉት 10 ተከታታይ የስራ ቀናት እስከ ቀኑ 9:00 እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በጨረታው መሳተፍ የሚፈልግ አልሚ የቦታውን ዝርዝር መረጃ ቅዳሜ ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም ታትሞ በሚወጣው አዲስ ልሳን ጋዜጣ መመልከት ይቻላል፡፡
ምንጭ:- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ


















