የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር 26ኛውን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከ35ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ ጋር በማጣመር ማክበሩ ተገለጸ።
ባለፈው ዓርብ በተካሄደው መርሐ ግብር የአርክቴክቸርና የግንባታ ዘርፉን አሁናዊ ሁኔታ፣ የሙያውን እድገት፣ የባለሙያዎችን መብትና ደኅንነት እንዲሁም በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የአርክቴክቸር ሙያን ማሳደግ፣ የሙያ ሥነ ምግባርን ማስጠበቅ፣ የአርክቴክቸር ጥራትና የዲዛይን ደረጃዎችን ማሳደግ እንዲሁም የባለሙያዎችን መብትና ጥቅም ማስከበር ዋነኛ ዓላማዎቹ እንደሆኑ ተጠቅሷል።
ሆኖም በኢትዮጵያ የግንባታና የአርክቴክቸር ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ የውድድር ጫና፣ የሙያ አቅም ገደቦችና የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች እንዳሉ በመድረኩ ተነስቷል።
በተለይም ለፕሮጀክቶች የሚመደበው የገንዘብ መጠንና የፋይናንስ አቅም ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸር መቀነሱ፣ በአማካይ 0.4 በመቶ ገደማ መሆኑ በባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና እየፈጠረ መሆኑ ተገልጿል።
በተቃራኒው ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው በጀትና የጊዜ ገደብ በላይ እስከ 350 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ በማሳየት እየተጠናቀቁ መሆናቸውም በውይይቱ ተነስቷል።
ባለሙያዎች ሙያቸውን በነጻነት፣ በፈጠራና ከማንኛውም ተገቢ ያልሆነ ውጫዊ ጣልቃ ገብነት በተላቀቀ መልኩ ማከናወን እንደሚገባቸው አጽንኦት ተሰጥቷል።
ይሁን እንጂ የሙያ ሕጎችን ማስከበርና የባለሙያዎችን መብት ማረጋገጥ ረገድ አሁንም የሚሻሻሉ ክፍተቶች እንዳሉ ተመላክቷል።
ማኅበሩ ከመንግሥታዊ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የምርምር ሰነዶችንና የሙያ ማሻሻያ ሐሳቦችን በማቅረብ የአርክቴክቸር ሙያውን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ሁለተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መስፋፋትን ተከትሎ በሀገሪቱ ያሉ የአርክቴክቸር ባለሙያዎች ቁጥር ከ18 ሺህ እስከ 20 ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ቢገመትም፣ ከእነዚህ ሁሉ ባለሙያዎች መካከል ሁሉም በቀጥታ በሙያው ላይ እየተሰማሩ እንዳልሆነ ተገልጿል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ የሕንፃና የኮንስትራክሽን ዘርፍ የጥራት ደረጃውን እንዲጠብቅ፣ የባለሙያዎች መብት እንዲከበርና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ከውጭ ከሚመጡ ተወዳዳሪዎች ጋር በእኩልነት እንዲወዳደሩ ጠንካራ ተቋማዊ አሠራር፣ የሕግ ተፈጻሚነትና የሙያ ደረጃዎችን ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑ አፅንኦት ተሰጥቶታል።
የማኅበሩ 35ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ከዓመታዊ ጉባኤው ጋር መከበሩ የሙያውን የቆየ ጉዞ ለመገምገም፣ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመለየትና ለቀጣይ የሙያ እድገት አቅጣጫ ለማስቀመጥ አስፈላጊ መድረክ ሆኗል።
ምንጭ:- ጌጡ ተመስገን
















