በቀን ከ300 በላይ ዘመናዊ በሮችን የሚያመርተውና በኮምቦልቻ የብረታ ብረት ምርቶች ኢንዱስትሪ (KOSPI) ስር የሚተዳደረው ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
በኦሮሚያ ክልል፣ ሸገር ከተማ፣ ገላን ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ዘመናዊ የበር ማምረቻ ፋብሪካ የሚድሮክ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የመንግስት አመራሮች፣ አባገዳዎችና ሃደሲንቂዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
አዲሱ ፋብሪካ በ8400 ካሬ ሜትር ላይ ማረፉ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀን ከ300 በላይ ዘመናዊ በሮችን እንደሚያመርት ተነግሯል።
ድምጽን የማያስተጋቡና ለሦስት ሰዓታት ያህል የእሳት አደጋን የሚቋቋሙት እነዚሁ በሮች፣ ዓለማችን የደረሰችባቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት ያካተቱ ስለመሆናቸው ተብራርቷል። በሮቹ በጣት አሻራ ወይም በካርድ አማካይነት የሚከፈቱ ሲሆን፣ ደጅ የቆመ ዕንግዳን ከቤት ውስጥ ሆኖ ለመመልከት የሚያስችሉ ዘመናዊ ካሜራዎች በበሮቹ ላይ እንደተገጠሙ ተጠቁሟል።
በሮቹ ከ30 በላይ የዲዛይን እና ከ20 በላይ የቀለም አማራጮች እንዳሏቸው በመርሐ ግብሩ ላይ ተጠቅሷል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሮቹ ከ6 እስከ 10 ተወርዋሪ እንዳላቸው ተገልጿል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አሕመድ በበኩላቸው፣ ኩባንያው የግንባታ ማጠቃለያ (ፊኒሺንግ) ለማከናወን የሚያግዙ ምርቶችን በማምረት የኮንስትራክሽን ዘርፉ የተጋረጠበትን ችግር እየቀረፈ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም፣ በእነዚሁ ምርቶች ላይ እያጋጠመ የሚገኘውን ዕጥረት ለመፍታት እንዲቻል፣ ሚድሮክ የአገር ውስጥ ግብዓቶችን በመጠቀም ምርቶቹን የመፈብረክ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አዲሱ የበር ማምረቻ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል ሲፈጥር፣ ሙሉ በሙሉ ፋብሪካው ስራ ሲጀምር ከ250 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድልን እንደሚፈጥር ለማወቅ ተችሏል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ከሚተዳደሩ ተቋማት አንዱ የሆነው ኮምቦልቻ የብረታ ብረት ምርቶች ኢንዱስትሪ (KOSPI) ተመስርቶ ወደ ስራ የገባው ጥር 27 ቀን 1992 ዓ.ም. ሲሆን፣ በኮምቦልቻ እና በሸገር ከተማ ሁለት ፋብሪካዎች አሉት።
ምንጭ፡ ጌጡ ተመስገን


















