“በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤት ገንብተን እናስረክባለን፤ በርካሽ ዋጋ መኪና አስመጥተን እንሰጣለን፤ በትንሽ ወለድ ብር እናበድራለን” በሚሉ አጓጊ ማስታወቂያዎችን በማስነገር፣ ቅድመ ክፍያ ከተቀበሉ በኋላ ውላቸውን ማክበርና ቃላቸውን መጠበቅ ያቃታቸው ተቋማት ጥቂት አይደሉም።
በዚህም በተናገሩት ልክ ሁነው ባለመገኘታቸው፣ ብዙዎቹ ለአመታት ለፍተው ያጠራቀሙትን ሀብት አጥተናል ሲሉ የሚደመጡ ብዙ ናቸው ።
በዚህ ዉዝግብ ምክንያትም ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሶ ጉዳዩ እልባት ያገኘም ፣ በክስ ሂደት ላይ የሚገኙም አሉ፡፡
ይህን መሰሉ ቃልን አለመጠበቅ ፣ ደንበኞችን ማጉላላትና ለኪሳራ መዳረግ መደጋገሙ በዘርፉ እና በማህበረሰቡ የመተማመን እሴት ላይ ከባድ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ማህበረሰቡ እርስ በእርስ ያለው ከፍተኛ መተማመን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰዎችን የሚያታልሉ አካላት እየበዙ ነው ያሉት የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያዋ ማስተዋል ስላይኑ ይህም ከገንዘብ ማጣት በላይ ለትውልድ የሚተላለፍ ጥልቅ ማህበራዊ ስብራትና ጠባሳ ነው ብለዋል።
በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ መተማመን ትልቅ ዋጋ አለው የሚሉት የ27 ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ ተባባሪ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስቻለው ታምሩ ፣ ይህ እምነት አንዴ ከተሸረሸረ ግን መልሶ ለማግኘት በጣም ከባድ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
ችግሩ በተጎዱ አካላት ላይ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ፣ ህግ አክብረው መስራት የሚፈልጉ እውነተኛ ተቋማትንም ማህበረሰቡ በጥርጣሬ እንዲያያቸው በማድረግ ጤናማ የንግድ ስርዓት እንዳይፈጠር እንቅፋት እንደሚሆን ባለሙያዎቹ አመላክተዋል።
ከአቅም በላይ ለማትረፍ ማሰብ ፣ ስለሚሰሩት ስራ በቂ ጥናት አለማድረግ ፣ ፈጣን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ለውጦችን እንዲሁም የአካባቢና የገበያ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ እቅድ ማውጣት ተቋማት ቃላቸውን እንዳያከብሩ ከሚያደርጓቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል እንደሆኑ አቶ አስቻለው ነግረውናል።
ስለሆነም ይህንን ድርጊት በጋራ መታገል እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ባለሙያዎቹ ፤ ወደ ገበያው የሚገቡ ተቋማትን በጥብቅ መፈተሽና አጭበርባሪዎችን በህግ ጠይቆ ተገቢውን ቅጣት መጣል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምንጭ:-ሸገር 102.1FM
















