የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ኢንጂነር ሔለን ታምሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾመ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢንጂነር ሔለን ታምሩ ገመዳን ከሥራ ብቃታቸው፣ ከሥነ ምግባራቸው እንዲሁም ከውጤታማነታቸው አንጻር የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ በእጩነት ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ እንዳመለከቱት፣ ዕድሜያቸው 33 ዓመት የሆነውና ቢሾፍቱ ከተማ የተወለዱት ኢንጂነር ሔለን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በውኃ ሀብት የመስኖ ምህንድስና፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሲቪል ምህንድስና እና በውኃ ሀብት ምህንድስና ያገኙ ናቸው።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የውል አስተዳደር ክትትል ኃላፊ ሆነው የሠሩ፣ በምህንድስና እና በፕሮጀክት አስተዳደር ለሰባት ዓመታት ያህል ያገለገሉ ሲሆን፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የመንገድ ሎጂስቲክስ ቢሮ ኃላፊ በመሆን በውጤታማነት ያገለገሉ ወጣት አመራር መሆናቸውን ከንቲባዋ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤትም የቀረበለትን እጩነት በመቀበል ኢንጂነር ሔለን ታምሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አድርጎ ሾሟቸዋል።
ሔለን ታምሩ (ኢ/ር) ከመስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት የኦሮሚያ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ቢሮን በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በሰጣቸው አዲስ ውሳኔ የከተማዋን የቤቶች ልማት ዘርፍ በበላይነት እንዲመሩ ተመድበዋል።
ኢንጂነር ሔለን ታምሩ በኦሮሚያ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ቢሮ በቆዩባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ተቋሙን ያለ እረፍት ቀንና ሌሊት ሲመሩ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ በዚህም የስራ ዘመናቸው በኮንትራት አስተዳደር፣ በመንገድ አስተዳደር፣ በሀብት አስተዳደርና በሰው ኃይል ዘርፎች ላይ መሰረታዊ ለውጦችን ማምጣት ችለዋል።
በተጨማሪም የተቋሙን አሰራርና የመዋቅር ሰንሰለት በየደረጃው በማደራጀት፣ የክልሉን ህዝብ በአገልግሎትና አስተዳደር ችግሮች ውስጥ በማሳተፍ፣ እንዲሁም በውል ትርጉምና ስምምነቶች ላይ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ በዘርፉ የመንገድ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በርካታ ስራዎችን አከናውነዋል።
ቀደም ሲል ሲያገለግሉበት የነበረው የኦሮሚያ መንገዶችና ሎጂስቲክስ ቢሮ ቤተሰቦች ባስተላለፉት የምስጋናና የደስታ መግለጫ፣ ኢንጂነር ሔለን ታምሩ ላበረከቱት የላቀ አመራርና አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ተቋሙ ለአዲሱ የስራ ዘመን መልካም ምኞቱን የገለጸ ሲሆን፣ አዲሱ አዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሾማቸውን የኃላፊነት ቦታ ተረክበው በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ስኬትና መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝቷል።
ምንጭ፦ Oromia Roads and Logistics Bureau


















