የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና IFC የመጀመሪያውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም ታሪካዊ ስምምነት ተፈራረሙ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የቤት መግዣ ብድር (Mortgage) ዘርፍ ውስጥ ታሪካዊ የተባለ የትብብር ስምምነት ተፈራረመ። ይህ ስምምነት በሀገራችን የመጀመሪያው የሆነውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ማዕቀፍ የሚፈጥር ነው።
በ100 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የተቋቋመው ይህ አዲስ ተቋም፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያገኝ ተገልጿል። ተቋሙ በዋናነት በባንክ ዘርፉ የሚታየውን የጥሬ ገንዘብ ፍሰት (Liquidity) አለመመጣጠን በመቅረፍ፣ የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስ በመላው ሀገሪቱ በሰፊውና በተደራሽ ሁኔታ እንዲቀርብ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ይህ አጋርነት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነቡና የዜጎችን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ ለተያዘው ሀገራዊ ግብ ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የተገለፀ ሲሆን፣ በፋይናንስ ስርዓቱ ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ያሰፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ስለ ስምምነቱ ባስተላለፉት መልእክት፣ ይህ አጋርነት ሀገሪቱ ያስቀመጠችውን የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ ግብ የሚያሳካ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ መገንባቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
















