የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ለ11ዱም ክ/ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽ/ቤት ህንፃዎች ከመንገድ መራት ያለባቸጡ ርቀት (Setback)፣ የመሬት ስፋት ዝቅተኛው ገደብ እና የህንፃ የጎን ስፋት (Frontage) አተገባበር መመርያ አስተላለፈ።
መስከረም 3 2017 ተፈርሞ ለሁሉም ክፍለ ከተሞች በተላለፈው በዚህ መመርያ መሰረት መሬቱ በሚያዋስነው መንገድ ስፋት መሰረት ግንባታ ለመገንባት የሚቻለው ከመንገድ መራቅ ያለባቸው ርቀት (setback) በሜትር 10, 5,3 እና 2ሜትር ነው።
እንዲሁም ከ15 ሜትር እና በላይ ስፋት ያላቸው መንገዶች የሚያዋስኗቸው ይዞታዎች ዝቅተኛው የቦታ ስፋት ሴት ባክ (set back) ከተቀነሰ በኋላ ቢያንስ 500 ሜትር ካሬ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል።
በሌላ በኩል በነዚህ መንገዶች ላይ ዝቅተኛው የህንፃ የጎን ስፋት (frontage) ከ20 ሜትር ያላነሰ መሆን አለበት ይላል።
የተላለፈውን መመሪያ ከታች ያገኙታል።

የተጣራ 500 ካሬሜ ጠቅላላ ስፋቱ ስንት ነው?
(ኢንጅነር ደሳለኝ እንደፃፈው)
በዚህ መመሪያ መሰረት 500 ካሬ ሜትር ሆኖ ለግንባታ ብቁ ለመሆን የፊት ለፊቱ ስፋት በትንሹ 20 ሜትር መሆን ስላለበት እሱን ይዘን በምሳሌ በቁጥር እናስቀምጥ።

ለምሳሌ አዋሳኝ መንገዱ 30 ሜትርና ከዛ በላይ የሆነ
- ከፊት ለፊት ለሴት ባክ የሚተው ትንሹ 10×20 (200 ካሬሜ) ይሆናል
- ተቀናንሶ ለግንባታ ብቁ ለመሆን የቦታው ስፋት በትንሹ 700 ካሬሜ (500 + 200) ሊሆን ይገባል። የፊት ለፊት ጎን ስፋቱም በትንሹ 20ሜ መሆን ይኖርበታል።
- የቦታው ስፋት ከ700 ካሬሜ በልጦ የፊት ለፊት ስፋቱ ከ20 ሜትር በታች ከሆነ የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት ብቁ አይሆንም ማለት ነው።
- ከፊት ለፊቱ በተጨማሪ ግራና ቀኝ መንገዳ ካዋሰነው ለset-back የሚቀናነሰው ስለሚጨምር የቦታው ስፋት ከወጪ ቀሪ 500 ካሬሜ ለመሆን በትንሹ የቦታው ስፋት 800 ካሬሜ ገደማ ሊሆን ይገባዋል ማለት ነው።
ማስታወሻ፦
- በዚህ መሰረት ለማሳያ ታሳቢ ላደረግነው ታሳቢ 500 ካሬሜ በትንሹ 700 ካሬሜ በካርታ ያለው ይዞታ መሆን ይኖርበታል ማለት ነው። ከዚህ መስፈርት በፊት 500 ካሬሜ ያለው ለሴትባክ ሲቀነስ ቀሪው በትልቁ 300 ካሬሜ ይሆናል።
- ሁለት መቶ ካሬ ያለው ካርታ እንጂ ለግንባታ የሚሆን መሬት የለውም።
- የይዞታው የጊቢው ርዝማኔ ከ10 ሜትር በታች ከሆነም ካርታ እንጂ ለግንባታ ብቁ የሚሆን መሬት የለውም።
በዚህ ስሌትና በወቅቱ ሴትባክ ህግ መሰረት በርካታ ቦታዎች ለግንባታ ብቁ ስለማይሆኑ አዋሳኝ ባለይዞታዎች ይዞታዎቻቸውን በማቀላቀል በጋራ ማልማትን ሊያስቡበት ይገባል።
የሌሎች ቦታዎችንም ይዘት አብሮ በተያያዘው የሴትባክ ህግ መሰረት እየሰሩ መረዳት ይቻላል።


















