መንግሥት የአገሪቱን የታክስ ገቢ ለማሳደግ የሪል እስቴት ንብረት ታክስ ለመጣል ማቀዱ ታወቀ።
መንግሥት በ2025 ታክሱን ተግባራዊ እንደሚደረግ በሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሰነድ ላይ የተቀመጠው ዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብር ያመለክታል።
መንግሥት ያቀደው አዲስ የሪል እስቴት ታክስ የሚጣለው በሪል እስቴት አልሚዎች ይሁን በገዢዎች ላይ ሰነዱ በግልጽ አያመለክትም። ነገር ግን የታቀደው የሪል እስቴት ታክስ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች እንዲሰበሰብ ታቅዶ በመረቀቅ ላይ ከሚገኘው የንብረት ታክስ በተጨማሪ የታቀደ አዲስ የታክስ ዓይነት መሆኑን ከሰነዱ ለመረዳት ተችሏል።
መንግሥት ዘንድሮ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረውና ለሦስት ዓመታት በሚቆየው ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ዘመን ውስጥ ሌሎች የታክስ ማሻሻያዎችንም ለማድረግ አቅዷል።
ከእነዚህም መካከል የተሽከርካሪ ዝውውር ታክስ፣ የግል ገቢ ግብር (የደመወዝ ግብር) የተመን መዋቅርን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሻሻል፣ የዊዝሆልዲንግ ታክስ ምጣኔዎችን (ዲቪደንድ ታክስና የሮያሊቲ ክፍያ ተመኖችን) ማሻሻል፣ በገቢ ዕቃዎች ላይ የተጣለውን ሱር ታክስ በሒደት ሙሉ በሙሉ ማንሳት፣ በሥራ ላይ የሚገኘውን የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ማሻሻል፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ መብቶችን ማሻሻል ይገኙበታል።
ሰነዱ እንደሚያስረዳው የውጭ ሀብት ወይም የውጭ ልማት ፋይናንስ ተደራሽነት ላይ እርግጠኛ የመሆን አዝማሚያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ፣ የአገር ውስጥ የታክስ ገቢ አሰባሰብን ማሻሻል ለሁለተኛ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በመሠረታዊነት አስፈላጊ አድርጎታል።


















