በረካ ሪል እስቴት (Bereka Real Estate) ባለፉት 8 ዓመታት ያከናወናቸውን የሪል እስቴት ልማት ሥራዎች፣ ያሳለፈውን የዕድገት ጉዞ እና በመጪዎቹ ዓመታት ለመተግበር ያቀዳቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ይፋ አደረገ።
ኩባንያው የዕድገት ጉዞውንና የወደፊት ዕቅዶቹን ያቀረበበት መርሐ ግብር ዛሬ ሕዳር 12 ቀን 2019 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኩባንያውን ስያሜ ትርጉም ያብራሩት የበረካ ሪል እስቴት ሥራአስኪያጅ አቶ አብዱልፈታህ አደም፣ “በረካ” የሚለው ስም ሰዎች በትዳራቸው፣ በሥራ ሕይወታቸውና በሀብት ንብረታቸው ውስጥ የሚመኙትን በረከት የሚወክል መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ አብዱልፈታህ እንዳሉት፣ ኩባንያው ባለፉት ዓመታት ከ14 በላይ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ከ305 በላይ የቤት ፈላጊዎችን የቤት ባለቤት አድርጓል። ከ250 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
በአሁኑ ወቅትም በ17 ፕሮጀክቶች ከ1,200 በላይ ቤቶችን እየገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኩባንያው በመጪዎቹ የልማት ዕቅዶቹ አካል በአዲስ አበባ ቄራ አካባቢ በ2,000 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚገነባ ዘመናዊ የንግድና የመኖሪያ አፓርትመንት ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።
በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረትና በሳርቤት አካባቢዎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፣ በካዛንቺስ አካባቢ በ2,000 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚያርፍ የመኖሪያና የንግድ አፓርትመንት ፕሮጀክትም መጀመሩን አቶ አብዱልፈታህ አስረድተዋል።
የድርጅቱ የማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ተመስገን ታምራት በበኩላቸው ድርጅቱ በ2011 ዓ.ም. በአንድ መሐንዲስና ከ6 እስከ 7 ሠራተኞች ብቻ ሥራ መጀመሩን፣ በአሁኑ ወቅት 16 መሐንዲሶችንና ከ250 በላይ ሠራተኞችን የያዘ ደረጃ መድረሱን አስረድተዋል።
በመጀመሪያው ፕሮጀክት በጋርመንት አካባቢ ባለ G+4 ሕንፃ 16 ቤቶችን በመገንባት ሥራውን የጀመረው በረካ ሆምስ፣ በቀጣይ ፕሮጀክቶቹን እያስፋፋ መምጣቱን ተመስገን ታምራት ገልጸዋል።
ድርጅቱ ባለፉት ዓመታት በሰፊ የማስታወቂያና የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ላይ ሳይመሠረት በተግባራዊ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የቤት ባለቤትነት ዕድል መፍጠሩንም አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በረካ ሪል እስቴት በ15 ሕንፃዎች ላይ የግንባታ ሥራ እያከናወነ ሲሆን፣ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ 1,000 የሚጠጉ ቤቶችን በሚቀጥሉት ከአንድ ዓመት እስከ 18 ወራት ውስጥ ለባለቤቶቻቸው ለማስረከብ ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በመጪዎቹ የፕሮጀክት ማስፋፊያዎች የሠራተኞቹን ቁጥር ከ400 በላይ ለማድረስ ማቀዱን ኃላፊው አስታውቀዋል።
በቤቶች ዲዛይንና ግንባታ ረገድም ድርጅቱ እስካሁን በተለይ ባለ ሦስት መኝታ ቤት ያላቸውን ቤተሰቦች ያማከሉ ቤቶችን በመገንባት ላይ ማተኮሩን ገልጸዋል።
ድርጅቱ በቀጣይ የግንባታ ሥራዎቹን በማስፋፋት ለተጨማሪ ዜጎች የቤት ባለቤትነት ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የሥራ ዕድል ማስፋፋትንም እንደ ዋነኛ የዕቅዱ አካል ማካተቱን ገልጿል።
በመጨረሻም የኩባንያውን የዕድገት ጉዞ አብረውት ላሳለፉ የበረካ ቤተሰቦችና ደንበኞች ምስጋና ያቀረቡት አቶ አብዱልፈታህ፣ የወደፊት አብሮነታቸውንም አረጋግጠዋል።
የበረካ ሪል እስቴት አራት አዳዲስ የሪል እስቴት ፕሮጀክቶች
በረካ ሪል እስቴት ኃ.የተ.የግ.ማህበር (PLC) በአዲስ አበባ በሚገኙ አራት ታዋቂ አካባቢዎች አዳዲስ የሪል እስቴት ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ዝግጅት ማድረጉን አቶ ተመስገን ታምራት ገልጸዋል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በቤተሰብ ተኮር የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት አቶ ተመስገን፣ በአዲሱ የልማት እቅድ ግን ለመኖሪያነትና ለኢንቨስትመንት የሚውሉ ንብረቶችን በፕራይም አካባቢዎች ላይ ለማልማት መወሰኑን አስረድተዋል።
አዳዲሶቹ ፕሮጀክቶች በቄራ፣ ካሳንቺስ፣ ሳርቤትና ጀርመን አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ለኪራይና ለኢንቨስትመንት ምቹ በሆኑ ስፍራዎች ላይ እንደሚገነቡ ተገልጿል።
በዕለቱ የበረካ ሪል እስቴትን ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ያሳለፈውን ጉዞ የሚያሳይ ዶክመንተሪ የቀረበ ሲሆን፣ ለተቋሙ ዕድገት አስተዋጽኦ ላደረጉ የምሥጋና ሠርተፊኬት ተሰጥቷል።
ምንጭ:- ድሬቲዩብ


















