በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ኦቪድ ግሩፕ ትብብር በአቃቂ ቃሊቲ ለሚገነባው 60 ሺህ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ መርሃ-ግብር ተካሄደ፡፡
በመርሃግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኦቪድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮናስ ታደሰ፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በ3 ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸው ፕሮጀክቱ፤ በኢትዮጵያ 7ኛው ትልቁ የከተማ ፕሮጀክት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ቤቶቹ ለ300 ሺህ ያህል ዜጎች መኖሪያ እንደሚሆንም ተነግሯል፡፡
የኦቪድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮናስ ታደሰ፤ አንገብጋቢ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ድርጅታቸው በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ዜጎችን የሚጠቅም እንደሆነ ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ዕድልም እንደሚመቻች ጠቁመዋል፡፡

የሚገነባው ከተማ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ ዘመናዊና ጥራቱን የጠበቀ እንደሚሆን ተመላክቷል። የ60ሺህ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዘመናዊ የንግድ ማዕከላት፣ የጤና ተቋማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ በቂ የአረንጏዴ እና የህጻናት መጫወቻ ስፍራዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እንዲሁም ዘመናዊ የመሰረተ ልማት የተሟላለት ከተማ አከል መንደር ሲሆን፣ ለ250 ሺሕ ነዋሪዎች የስራ እድል ይፈጥራል።

















