በአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ ጸደቀ ፤ ሕገ-ወጥ «የመንደር እና የአካባቢ ውሎች » በጥብቅ ተከለከሉ፡፡
ከዚህ ቀደም የወጣውን የከተማ ፍትሐዊ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1320/2016 መነሻ በማድረግ፣ ለ2019 በጀት ዓመት የሚተገበረው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% መሆኑን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።
ዋጋ ጭማሪውና የውል እደሳቱ መነሻ የሚሆነው ከዚህ ቀደም በነበረው ውል ላይ የተቀመጠው የኪራይ ዋጋ ብቻ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
በመላው ከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ-ተከራይ አዲስ የውል እድሳት ምዝገባ ከዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ መተግበር ጀምሯል።
የተጣሉ ጥብቅ ክልከላዎችና ሕጋዊ እርምጃዎች
አዲሱን የውል እድሳት ምዝገባና የተቀመጠውን የዋጋ ጣሪያ ወደ ጎን በመተው የሚፈጸሙ ማናቸውም ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ ጥብቅ ክልከላ ተጥሏል።
በዚህም መሠረት፡-
በቢሮው ከተመዘገበውና ከሚመዘገበው ውል እንዲሁም ከሚሰጠው አቅጣጫ ውጭ፣ «ልዩ ውል» በሚል የሚፈጸሙ ማናቸውም የመንደር ውሎች፤
ከሕጋዊው አሰራር ውጭ የሚደረጉ የአካባቢ ውሎች፤
በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) አካባቢ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ውሎች ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ መሆናቸውን ቢሮው አስገንዝቧል።
ማንኛውም አከራይ እና ተከራይ እነዚህን የተከለከሉ ሕገ-ወጥ ውሎች ይዘው ሲገኙ ወይም ከተቀመጠው የ11.5% የዋጋ ጭማሪ ጣሪያ በላይ ፈጽመው ከተገኙ፣ ቢሮው አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በይፋ አሳስቧል።
update (09/07/2026)
በአከራይ ተከራይ ውል የሚከተሉትን ተግባራት መፈጸም የተከለከለ ነው።
- የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ሳያስመዘግቡ መከራየትና ማከራየት፤
- የውል እድሳት ምዝገባን አለመፈጸም በአከራይ ወይም ተከራይ ቸልተኝነት ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ የተጀመረውን አዲስ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እድሳት ምዝገባ ሳያከናውን መቅረት ወይም መሸሽ አይቻልም።
- የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል ዕድሳት አለማስመዝገብ፤
- ሕገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ በከተማ አስተዳደሩ ከተቀመጠው የ11.5% ዓመታዊ የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ በላይ መጨመር ወይም በየምክንያቱ ዋጋ ማናር በጥብቅ የተከለከለ ነው።
- አዋጁ ከሚፈቅደው ውጪ የውል ዘመን ሳይጠናቀቅ ከቤት ማስወጣት፤
- በአዋጁ የተቀመጠውን የማስታወቂያ ወይም የማስጠንቀቂ ጊዜ ሳይሰጥ ውል ማቋረጥ፤
- አዋጁ ላይ ከተቀመጠው መጠን በላይ የቅድመ ክፍያ እንዲፈጸም ማስገደድ፤
- በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ የሆነ የኤሌክትሮኒክስ መንገድ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ክፍያ አለመፈጸም፤
- ቀደም ሲል ሲከራይ የቆየ የመኖሪያ ቤት ወይም ግንባታው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀ አዲስ መኖሪያ ቤት ያለአገልግሎት
እንዲቀመጥ ማድረግ፤ - የመንደር ወይም የ«ልዩ» ውል ማሰር፦ በየደረጃው በሚገኙ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ፅህፈት ቤቶች ሳይመዘገብና ዕውቅና ሳይሰጠው፣ በአከራይና ተከራይ መካከል ብቻ የሚደረግ ማናቸውም ዓይነት “የመንደር ውል” ወይም “የውስጥ ስምምነት” በሕግ ፊት ዋጋ የለውም፤ የተከለከለም ነው።
- በጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) አካባቢ የሚደረጉ ሕገ-ወጥ ውሎች በኮንዶሚኒየም መንደሮች ውስጥ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን ያለ ቢሮው ዕውቅናና ምዝገባ በሕገ-ወጥ መንገድ ማከራየትና ውል መዋዋል የተከለከለ ነው።
update (13/07/2026)
ማንኛውም የመኖሪያ ቤት አከራይና ተከራይ በውል እድሳት ወቅት ማሟላት ያለባቸው:-
- የቤት ካርታ
- ቀደም ሲል የነበራቸውን የውል ስምምነት ሰነድ፤
- ኪራይ ሲከሉበት የነበረው የኤሌክትሮኒክስ የክፋያ ሠነድ፤
- የአከራይ እና የተከራይ የዲጂታል መታወቂያ፣ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የመስሪያ ቤት መታወቂያ፣ መንጃ ፍቃድ፣ ፓስፖርት፣ የጠበቃ ፍቃድ፣ የሰራተኞች ጡረታ መታወቂያ፣ የዩኒቨርሲቲ ወይም ኮሌጅ ተማሪ፣ የሙያ ስራ ፍቃድ ኦርጅናል ኮፒ፤
- የመኖሪያ ቤት ውሉን የሚያድሰው በወኪል ከሆነ ህጋዊ ውክልና፤ ኦርጅናል እና ኮፒ ይዘው መገኘት አለባቸው።
update (13/07/2026)
« በአከራይ ተከራይ ውል እድሳት ሕጋዊ አሰራርን መጣስ በሕግ ያስቀጣል ! »
የከተማ አስተዳደሩ የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ማድረጉን ተከትሎ፣ አንዳንድ አከራዮች ሕጋዊ አሰራሩን ለመጣስ እያደረጉት ያለው ሙከራ በተለያዩ ጥቆማዎች ለቢሯችን ደርሰዋል፡፡
ከደረሱን ጥቆማዎችም በተከራዮች ዘንድ ምሬት ከፈጠሩ ምክንያቶች መካከል እንዳንድ አከራዮች ቤቱን ለራሴ ወይም ለዘመዴ ፈልጌዋለሁ በሚል ተከራዩን በሐሰተኛ ምክንያት አስለቅቆ አዲስና ሰማይ የነካ ዋጋ መጫንና በዚያው ላይ የ11.5% ጭማሪ ጥሎ ሕጋዊ ማስመስል አንዱ ሲሆን ፤
ድርብ ውል በማስፈረም በአፍ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ተስማምቶ በሰነድ ላይ ግን ከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው የ11.5% ጣሪያ ብቻ እንዲፈርሙ በማድረግ የሚፈፀሙ የህግ ጥሰቶች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው።
በመሆኑም ተከራዮች በአፍ የተጋነነ ዋጋ ተጠይቃችሁ ውል ላይ ግን ዝቅተኛ ከተጻፈ፣ ክፍያውን ሁልጊዜ በባንክ ብቻ በማስተላለፍ ሕገ-ወጥነቱን በማስረጃ እንድታረጋግጡ ቢሮው ያሳስባል፡፡
አንዳንድ ህግ የምትጥሱ አከራዮችም መተሳሰብን ፤ መተዛዘን እና ሰብአዊነትን ቢሮው አስቀድሙ እያለ ሕግ ጥሰው በተገኙ አካላት ላይ ግን ከባድ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ቅጣት እንደሚጣል ቢሮው በጥብቅ ያሳስባል፡፡
መላው ማህበረሰብም ይህንን «ሕጋዊ አሰራርን የመጣስ» ተግባር በጋራ ለመዋጋት ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
update ሀምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም
የመኖሪያ ቤት አከራይ ተከራይ ውል እድሳት እስከ ነሀሴ 30 /2018 ዓ.ም ድረስ ተራዘመ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ እና በኪራይ ገበያው ላይ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥና ዘፈቀዳዊ አሰራሮችን በዘላቂነት ለመግታት እየወሰደ ባለው እርምጃ የቤት ኪራይ ጭማሪ ጣሪያ 11.5% ሆኖ መወስኑን ተከትሎ የውል እድሳት ምዝገባም ከ ሐምሌ 1 / 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህንን ተከትሎ በመላው ከተማዋ የሚገኙ የግል መኖሪያ ቤቶች የአከራይ-ተከራይ የውል እድሳት ምዝገባ ግዜ እስከ እስከ ሀምሌ 30 /2018 ዓ.ም የነበረው እስከ ነሀሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አሳውቋል።
የውል እድሳት ግዜው በህብረተሰቡ ጥያቄ መስረት የተራዘመ ሲሆን ነዋሪው ያለምንም መጨናነቅ እንዲዋዋል ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል።
ህብረተሰቡ በሁሉም ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ፅ/ቤት ፤ በየወረዳው በተዘጋጁ የውል ቦታዎች እና በሁሉም ክፍለ ከተማ አዲስ መሶብ አስፈላጊውን መረጃ ይዞ በመገኘት አገልግሎቱን ማግኘት የሚቻል መሆኑን ቢሮው በድጋሚ ያሳውቃል፡፡
update (01/13/2018)
የአከራይና ተከራይ ውል እድሳት ማጠናቀቂያ የጊዜ ገደብ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ለመጨረሻ ጊዜ ተራዝሟል፡፡
ከሀምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የአከራይና ተከራይ ውል ምዝገባና እድሳት አገልግሎት ለመጨረሻ ጊዜ እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው የውል ምዝገባና እድሳት ስራው እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ ጊዜ ገደብ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፣ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በጊዜው አሟልተው ያልቀረቡ፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ በልዩ ልዩ ምክንያት ከአዲስ አበባና ከሀገር ውጭ የነበሩ ተዋዋዮች መኖራቸውን ተረድቷል።
በህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ መሰረት የመጨረሻ ተጨማሪ እድል መስጠት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ቢሮው ገልጿል።
በመሆኑም እስከ ዛሬ ውላቸውን ያላደሱ ሁሉም አከራዮችና ተከራዮች ይህንን የመጨረሻ እድል በመጠቀም እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በክፍለ ከተሞች፣ በሁሉም የመሶብ አንድ ማዕከላት እና ለዚሁ አገልግሎት በተዘጋጁ ቦታዎች በመቅረብ ውላቸውን እንዲያድሱ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
ምንጭ: የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ


















