በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከምትክ ካሳ ጋር በተገናኘ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የከተማዋ ፍትህ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ደጄኔ ቢሮው የምትክ ካሳ ክፍያን በተመለከተ ህግ መኖሩ እና ግልፅ መመሪያ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ ምትክ ካሳ ክፍያ እንደ ቦታው ስፋትና ግንባታው የተሰራበት የግብአት አይነትን ተከትሎ ካሳ ክፍያ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በምትክ ካሳ ክፍያው ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ከመመሪያው ባሻገር ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጣ ግብረ ሀይል መቋቋሙን አመላክተዋል፡፡ የግብረ ሀይሉ መቋቋም ችግሩን ለመከላከል ሌላኛው መንገድ ይሆናል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ምትክ ቦታ አላገኘንም የሚል ቅሬታ እስካሁን አልቀረበም ብለዋል፡፡ የከተማዋ ፍትህ ቢሮ በካሳ ክፍያ ሂደት ብልሹ አሰራር እንዳይፈጠር መመሪያ መዘጋጀቱን ቢያሳውቅም መናኸሪያ ሬዲዮ ከአንዳንድ ምንጮቹ እንደሰማዉ የተሰሩበትን ግብዓት ጡብ እና ብሎኬት አድርጎ በመመዝገብ ተጨማሪ ክፍያ ያለ አግባብ እንዲከፈል እየተደረገ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ፍትህ ቢሮም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ማቅረብ ለሚፈልግ አካል በሩ ክፍት መሆኑን አስታዉቋል፡፡
ምንጭ፦ መናኸሪያ ሬዲዮ


















