በአዲስ አበባ ከተማ መንግሥት መሬት ለልማት በመፈለጉ ምክንያት ቤት የፈረሰባቸውና ከቦታቸው የተነሱ ግብር ከፋዮች፣ በተከፋፈለ ጊዜ እንዲከፍሉ እያደረገ መሆኑን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው ስለክፍያ አፈጻጸሙ ያስታወቀው የታክስ ውሳኔ ቅሬታን በተመለከተ ጥር 4 ቀን 2018 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጥ ነው፡፡
የገቢዎች ቢሮ ኪሳራም ሆነ ሌሎች ችግሮች ያጋጠሟቸው የግብር ዕዳ መክፈል የማይችሉ ግብር ከፋዮች፣ ተጨማሪ የመክፈያ ጊዜ በመስጠት፣ ዕዳቸው ተሸንሽኖ በሚሰጣቸው ጊዜ እንዲከፍሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የተናገሩት የቢሮው የታክስ ዕዳ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ንብረት በሪሁን ናቸው፡፡
‹‹በግብር ሕጉ መሠረት በተለያዩ ምክንያቶች በአንዴ ግብር መክፈል ለማይችሉ ሰዎች፣ ለመክፈያ የተራዘመ የጊዜ ዕድል በመስጠት ድጋፍ እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡
የታክስ ዕዳ አስተዳደር ዳይሬክተሩ አክለውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሮ ክስተቶች የተጎዳበት ሰው ታክስ ለመክፈል የማይችል ከሆነ፣ የተጣለው ቅጣት ትክክል ቢሆንም እንኳ ቅጣቱን በማንሳት በንግድ ሥርዓቱ ሊቀጥል እንዲችል የመደገፍና የማበረታታት ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም ግብር ከፋዩ በአንድ ጊዜ ክፈል ቢባል ከታክስ መረቡ ሊወጣ ስለሚችል፣ መንግሥት ግለሰቦችን ለመጥቀም ሲል የሚፈጽመው የክፍያ ስምምነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ በእሳት አደጋ የተቃጠለባቸው፣ ፅኑ ሕመም ውስጥ የሚገኙ፣ ሕይወት ያለፈ ከሆነና የንብረት ወራሹ የዕዳው ተፅዕኖ ከፍተኛ ሆኖበት ለችግሩ ማረጋገጫ ካቀረበ፣ የግብር ቅጣቱ በልዩ ሁኔታ የሚነሳበት አሠራር መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ በሚገኙ 17 ቅርንጫፎች ባለፉት ስድስት ወራት 13,643 ቅሬታዎች ቀርበው 11,892 ለሚሆኑት ምላሽ መሰጠቱን የገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የታክስ ውሳኔ ቅሬታ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ ጽጌ ናቸው፡፡
ለ1,518 ቅሬታዎች መልስ አለመሰጠቱን፣ ምላሽ የተሰጣቸው ግብር ከፋዮች አንድም ለቀረበው ቅሬታ መረጃን በማጣራት ተቀባይነት ካገኘ ውሳኔ መስጠት በሌላ በኩል የታክስ ውሳኔውን ማፅናት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወደ አምስት ሺሕ የሚጠጉ ቅሬታዎች ተቀባይነት አልነበራቸውም ብለው፣ በ230 ሰዎች ቀርበው የነበሩ ቅሬታዎች በራሳቸው ጊዜ ሲቋረጡ፣ ሰባት ሺሕ የሚጠጉት ደግሞ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የመንግሥትን ገቢ በማስፋት ሒደት ውስጥ በቫት ምዝገባ የቀን ገቢ ግምት አሠራር፣ እንዲሁም በመርካቶ ገበያ ውስጥ የሽያጭ መመዝገቢያ ላይ በተደረገ ቁጥጥር ቅጣት መጣልን ተከትሎ የታክስ ቅሬታዎች መጨመራቸው ተገልጿል፡፡
የቀን ገቢ ምንም እንኳ ግምት ቢሆንም፣ ግብር ከፋዩ ሲጠየቅ የሚሰጠው መረጃ ግልጽ ካልሆነ፣ የቢሮው ሠራተኞች ለቀን ገቢ ግብር አመልካች የሆኑ የራሳቸውን መሥፈርት ይጠቀማሉ ያሉት አቶ ኤርሚያስ፣ ይሁን እንጂ ግብር ከፋዩ ያላግባብ የተጣሉበት ግብሮች ሲኖሩ መብቱን ተጠቅሞ ቅሬታውን ቢያቀርብ ስህተቶች ካሉ ይሻሻላሉ ብለዋል፡፡
ምንጭ: Ethiopian Reporter


















