ቤት ለሚገዙ እና ለሚሸጡ አካላት ማሳሰቢያ ተሰጠ

በአሁን ግዜ ቤት የሚገዙ፣ የሚሸጡ ሁሉ ስራቸው ህገወጥ ስለሆነ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት አሳስቧል።
.
የቋሚ ንብረት ሽያጭ የቆመ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎቱ ሳይጀመር ሽያጭ እና ማስተላልፈ በመንደር ውል እና በውክል እየተሰራ መሆኑ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ዘግቧል።

የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ፤ በውክልናም ሆነ በመንደር ውል የቤት ሽያጭ ማከናወን ህጉ እንደማይፈቅድ ገልፀዋል።
.
አገልግሎቱ የሚጀምርበትን ጊዜ እናሳውቃለን ብለዋል።

” ቤት ሽያጭ ውል ሰነድ የማረጋገጥ አገልግሎት ነው ” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ” ይህ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል። ተቋሙ በተለይ ከአ/አ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ህገወጥ ይዞታዎችን የማረጋገጥ ስራ እየሰረ ስለሆነ ከዛ ጋር ተያይዞ ላልተገባ ሰዎች ያልተገባ ውል ውስጥ እንዳይገቡ ያን የማረጋገጥ ስራ እስኪጠናቀቅ በጊዜያዊነት አገልግሎቱን መስጥ ቆሟል ” ሲሉ አስረድተዋል።

ይሄ ህገወጥ ይዞታዎችን የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉቀን ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ላልተወሰ ጊዜ የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም መኖሪያ ቤት ሽያጭ / በስጦታ የማስተላለፍ ውሉ አሁንም ለጊዜው እንደተቋረጠ ይቀጥላል ሲሉ አሳውቀዋል።

ተቋሙ የተቋረጠውን አገልግሎት በሚጀምርበት ሰዓት በግልፅ በተለያየ ሚዲያ መረጃውን የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይ የተጠራቀመ አገልግሎት ካለ ተገልጋዮች በሰልፍ ብዙ ሳንይገላቱ ለመስራት አሰራር ተዘርግቶ ይኬዳል ሲሉ ጠቁመዋል።

ህብረተሰቡ ላልተገባ የመንደር ውል ሆነ ባልተገባ መረጀ ላይ ተመስርቶ ከሚደረጉ ውሎች እንዲቆጠብ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት ለሸገር ራድዮ በሰጠው ቃል አሳስቧል።

ምንጭ: Sheger FM

Share to your Network: