ኖህ ሪል እስቴት በአዲስ አበባ ከተማ በሴቶች አደባባይ ኖህ ቪክትሪ ሳይት የተገነቡ የመኖሪያ አፓርታማዎችን ለደንበኞቹ አስረክቤአለሁ በሚል በመገናኛ ብዙሃን ያሰራጨው ዜና ሐሰት መሆኑንና ቤቱን ከውል ጊዜው ከአራት ዓመት በላይ ቢያልፍም መረከብ አለመቻላቸውን ቤት ገዥዎች ተናገሩ።
ኖህ ሪል እስቴት ቅዳሜ ግንቦት 1/2018 ዓ.ም መገናኛ ብዙሃን በተገኙበት ለቤት ገዥዎች አስረክቤአለሁ ካላቸው ቤቶች በየካ ክፍለከተማ ወረዳ ስድስት ክልል ውስጥ በተለምዶ አቧሬ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የተገነባው አፖርታማ ይገኝበታል።
ቤት ገዥዎቹ ለድሬቲዩብ እንደገለጹት ከኖህ ሪል ስቴት የሚጠበቅባቸውን ፈጽመው የመኖሪያ ቤት መግዛታቸውን አስታውሰዋል።
ገዥዎቹ በአቤቱታቸው እንደጠቀሱት “እኛ አቤቱታ አቅራቢዎች በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ክልል ውስጥ በካርታ ቁጥር የ16/99370/09 የቤት ቁጥሩ 394 የቦታ ስፋቱ1,850 ካሬ ሜትር ላይ ከሚገነባው ህንፃ የመኖሪያ አፓርትመንት ቤት በተናጥል በተፈረመ ውል፤ ውሉ በተፈረመ በሰላሳ ስድስት ወራት/በሶስት ዓመት/ የቤቶቹን ግንባታ አጠናቆ ሊያስረክበን ተዋውለን ነበር።
በውላችን መሰረት የሚጠበቅብንን ክፍያ ከፍለን ያጠናቀቅን ቢሆንም በውሉ ከተጠቀሰው የማስረከቢያ ጊዜ ከአራት ዓመት በላይ ሊያስረክበን አልቻለም።
ይኸ እውነታ ግልዕ ሆኖ እያለ አልሚው (ሻጭ) የመኖሪያ አፓርትመንቶቹን ግንባታ አጠናቆ ያስመረቀ እና ለገዙት ደንበኞች ቤቶቹን በማስረከብ ላይ መሆኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ( የመንግስት ሚዲያዎችን ጨምሮ) እየገለፀ መኾኑ ግራ አጋብቶናል ብለዋል።
አያይዘውም እኛ ገዥዎች የግንባታ ግዜው በመራዘሙ እና በውላችን መሰረት ቤቱን ሊያስረክቡን ባለመቻሉ ለከፍተኛ ወጪ/ለመኖሪያ ቤት ኪራይ እና የተለያዩ ወጪዎች/ እና እንግልት ተዳርገናል ብለዋል።
ኖህ ሪል እስቴት መገናኛ ብዙሃንን ጠርቶ ቤቶችን ለገዥዎች
አቤቱታ አቅራቢዎቹ አያይዘውም ከዛሬ ነገ የመኖሪያ አፓርትመንታችን እንረከባለን ብለን በተስፋ እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት ከአራት ዓመት መዘግየት በኋላ በቀን 03/09/2018 ዓ.ም. በደብዳቤ ቁጥር NOH/G09/250/18 በተፃፈ ደብዳቤ ከውላችን ውጭ የገዛነውን ቤት የጋራ መጠቀሚያ ቦታ ጭማሪ ክፍያ መኖሩን በመግለዕ ለዚሁ ጭማሪ ተጨማሪ ክፍያ እንድንከፍል ጠይቆናል።
በእኛ እምነት መንግስት በአካባቢው በሰራው የኮሪደር ልማት ምክንያት አካባቢው የተሻሻለ በመሆኑ ይህንን እንደምክንያት በመጠቀም የእኛን በድምሩ ከ7 ዓመት በላይ መጠበቅ ከምንም ሳይቆጠር አግባብነት የሌለው ጥቅም ለማግኘት እየሞከረ መሆኑ አሳዝኖናል ካሉ በኋላ ሪል ሪል እስቴቱ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያና እንግልት ቤታቸውን እንዲያስረክባቸው ጠይቀዋል።
የኖህ ተለዋዋጭ ምላሾች
ሪል እስቴት በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ሆኖም በተጠቀሰው ቦታ የገነባውን ቤት ርክክብ መፈጸሙ መናገሩን ግንቦት 1/2018 ዓ.ም የሰጠውን ይፋዊ መግለጫ ተከትሎ ድሬቲዩብን ጨምሮ በተለያዩ ማኀበራዊ ሚድያዎች የተሰራጩ ዘገባዎችን ለመመልከትና ለመረዳት ችለናል።
በተጨማሪም ትልቁ የመንግስት ልሳን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይኸንኑ የገዥዎች ቅሬታ መነሻ በማድረግ የካቲት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በኖህ ሪል ስቴት እና አጋር ኩባንያዎች የሕግ እና የደንበኞች አገልግሎት ጉዳይ ክትትል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ደስታን አነጋግሮ ያቀረበውን ዘገባ ተመልክተናል።
ኃላፊው በምላሻቸው ርክክቡ ሳይፈጸም መዘግየቱን በማመን በይፋ ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ለርክክቡ መጓተት ምክንያት ነው ያሉት የህንፃው የፍሳሽ ስርዓት አለመጠናቀቅንና ጉዳዩም ከአቅማቸው በላይ ሆኖ መቆየቱን የሚጠቅስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ችግሩም ጊዜያዊ መፍትሔ ማግኘቱን በመጥቀስ “ጊዚያዊ ሴፕቲክ ታንክ መዘጋጀቱንና አነስተኛ ስለሆነ በየቀኑ እያስመጠጡ መጠቀም ይችላሉ” ብለዋል።
በተጨማሪም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ቤቱን እንደሚያስረክቡ ቃል መግባታቸው ተዘግቧል።
ኖህ ይኸን መግሐጫ ከሰጠ እና ግንቦት 1/2018 ዓ.ም ለደንበኞቹ ቤቶቹን ማስረከቡን በመገናኛ ብዙሃን ካስነገረ በኋላ ለቤትገዥ ደንበኞቹ ግንቦት 3/2018 ዓ.ም ደብዳቤ ፅፏል።
በዚህም ደብዳቤው የጋራ መጠቀሚያ ቦታ ጭማሪ ክፍያ መኖሩን በመግለዕ ለዚሁ ጭማሪ ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉት ጠይቋል።
የሕግ ባለሙያ አስተያየት
ስሜ አይገለፅ ያሉ በማናቸውም ፍ/ቤት በጥብቅና ሙያ በማገልገል ላይ የሚገኙ የሕግ ባለሙያ አጭር አስተያየት ሰጥተዋል።
ጉዳዩን በቅርበት መመርመራቸውን በማንሳት አልሚው ከዓመታት መዘግየት በኋላ ቤቱን ላለማስረከቡ የሚሰጣቸው ተለዋዋጭ ምክንያቶች ውሃ የማያነሱ ናቸው ብለዋል። አራት ዓመት ካዘገዩ በኋላ ሚዲያ ጠርቶ ቤቱን ሳያስረክብ አስረክቤአለሁ ብሎ ሐሰተኛ መግለጫ መስጠት፣ “የፍሳሽ ችግር አጋጠመን” እንዲሁም “የትርፍ ቦታ ክፈሉኝ” የሚሉ ተለዋዋጭ ምክንያቶችን መስጠት ጊዜ ለመግዣ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት የህግ መሰረት የላቸውም።
አለመግባባቱ ለአልሚው መልካም ስምም የሚጠቅም ባለመሆኑ ጉዳዩ ወደፍርድ ቤት ኼዶ የሚዲያዎች ዜና ከመሆን በፊት ፈጥኖ ቢያርም ይበጀዋል በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል።
ምንጭ: ጌጡ ተመስገን


















