በፍሊንትስቶንስ አ.ማ(Flintstone) እና በደንበኞቹ መካከል 2 ዓመት በላይ ሲያከራክር የቆየው ጉዳይ በፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት መቋጫ አገኘ።
በብያኔው መሰረት ፍሊንትስቶንስ አክስዮን ማህበር ለቀድሞ ደንበኞቹ ከ 282 ሚሊየን ብር በላይ የካሳ ክፍያ የሚከፍል ይሆናል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቀን 08/11/18 ዓም በዋለው ችሎት፣ “ፍሊንትስቶንስ ኢንጅነሪንግ አ.ማ”(በአሁኑ ስያሜ ፍሊንትስቶንስ አ.ማ) ከድርጅቱ ቤት ገዝተው ግንባታ ርክክብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ክስ የመሠረቱ 212 ደንበኞችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በግልግል ዳኝነት ጉባኤ የተሰጠውን ውሳኔ አጽንቷል።
ጉዳዩ የተጀመረው ፍሊንትስቶንስ ኢንጅነሪንግ አ.ማ. ከ2008 እስከ 2009 ዓም ከደንበኞቹ ጋር በገባቸው የቤት ግዥ ውሎች መሠረት፣ ቤቶቹ በተባለው ጊዜ ውስጥ ርክክብ ባለማድረጋቸው ነው።
ደንበኞቹ ቤት ገንብቶ በመሸጥ የሪልስቴት ስራ ላይ ከተሰማራው ፍሊንትስቶንስ ሆምስ አ.ማ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በለሚ ኩራ ክፍለከተማ “ቦሌ በሻሌ” በተባለ ሳይት የጋራ መኖሪያ ቤት ህንጻ ገንብቶ እንዲያስረክባቸው በውል ስምምነት ግዢ ፈጽመዋል።
በውሉ መሠረት የቤት ርክክቡን ደንበኞቹ ግዢ ከፈጸሙበት አመት ጀምሮ በሚታሰብ 28+2 ወራት ውስጥ ሊፈጸም ቢገባም፣ ድርጅቱ ግንባታውን በተደጋጋሚ በማጓተቱ ደንበኞቹ ለረጅም ዓመታት ርክክብ ሳያገኙ ቆይተዋል።
ከሳሽ ደንበኞች የቤት ግዢውን የፈጸሙት ከ 2008 ዓም እስከ 2009 ዓም ባሉት የተለያዩ ጊዜያት ቢሆንም ፍሊንትስቶንስ ጋር በገቡት ቤት ገንብቶ የመሸጥ የውል ስምምነት መሰረት በተሰጠው የኮንትራት ጊዜ ገንብቶ ሊያስረክባቸው አልቻለም።
ይህንን ተከትሎ 212 ከሳሾች (ቤት ገዢዎች) በጋራ በመሆን ጉዳዩን ወደ ግልግል ዳኝነት ጉባኤ ወስደው ክስ መሥርተዋል።
ጉዳዩን የተመለከተው የግልግል ዳኝነት ጉባኤ ከሁለቱም ወገኖች ማስረጃና ክርክር ከሰማ በኋላ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዝርዝር ብይን ሰጥቷል።
ጉባኤው በውሳኔው መሠረት፣ ድርጅቱ በውሉ የተገባውን የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜ ገደብ (ከውል ፊርማ በኋላ ባሉት የተለያዩ የግንባታ ደረጃዎች ልክ ማለትም መሠረት ስራ 15 ወራት፣ ሁለተኛ ደረጃ ግንባታ ተጨማሪ ወራት፣ እና የመጨረሻ ርክክብ ጊዜ) ማክበር ሲገባው ባለማክበሩ፣ ደንበኞቹ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው አረጋግጧል።
በጉባኤው ፍሊትስቶንስ አክስዮን ማህበር ግንባታውን በኮንትራቱ መሰረት ገንብቶ ማስረከብ ያልቻለው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በሰሜን በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የብር መግዛት አቅም መቀነስ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶችን ያቀረበ ቢሆንም በጉባኤው ተቀባይነት አላገኘም።
በዚህም መሠረት፡-
- ለእያንዳንዱ ተከራካሪ ደንበኛ፣ በቤት ስፋት (በካሬ ሜትር) እና በውል ዋጋ ልክ የተሰላ የመዘግየት ካሳ እንዲከፈል፤
- አማካይ የካሬ ሜትር ዋጋ ብር 13,700.00 ላይ ተመስርቶ፣ ለእያንዳንዱ ቤት የተለያየ ስፋት (ከ41.08 እስከ 86.23 ካሬ ሜትር የሚደርስ) ተመጣጣኝ ካሳ እንዲሰላ፤
- በአጠቃላይ ለ212ቱም ከሳሾች ሲደመር (282 ሚሊየን 780ሺ ብር በላይ) የሚቆጠር ካሳ ተከሳሽ ድርጅቱ እንዲከፍል፤
- እንዲሁም ተጨማሪ ወለድና ተያያዥ ወጪዎች በህግ አግባብ እንዲተኩ ጉባኤው ወስኗል።
ውሳኔው ለእያንዳንዱ ከሳሽ በስም፣ በቤት ቁጥር እየተለየ በተናጠል በተሰላ የገንዘብ መጠን በሚመጣው መሰረት ክፍያው እንዲፈጸምለት ያዛል።
ከሳሾች በግልግል ጉባኤው ውሳኔ ባለመስማማት፣ ጉዳዩን በሰበር አቤቱታ ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወስደውታል።
ቤቶቹን የገዙ ግለሰቦች (ከሳሾች) ጉዳዩን ወደሰበር ሰሚ ችሎት የወሰዱት ድርጅቱ አሁን ያለውን የገበያ ዋጋ መሰረት ያደረገ የካሳ ክፍያ እንዲፈጽምልን የሚል ጭብጥ ያላቸው መሆኑን ተከትሎ ነው።
ከሳሾች ቤቱን በገዙበት ወቅት አማካይ የካሬ ሜትር ዋጋ 13,700 ብር የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት (ክሱ በተመሰረተበት) የገበያ ዋጋው ወደ 99,000 ብር ከፍ ማለቱን በመጥቀስ፣ በመካከሉ ያለውን የ85,300 ብር የዋጋ ልዩነት ተባዝቶ በካሳ መልክ እንዲከፈላቸው ተከራክረዋል።
በሌላ በኩል ተከሳሹ ድርጅት ቤቶቹን አጠናቆ ለማስረከብ በውል ማሻሻያ በካሬ ሜትር 24,500 ብር ጭማሪ እንዲደረግ ያቀረበውን ጥያቄ ሌሎች ገዢዎች ተቀብለው ቤታቸውን እየተረከቡ ባለበት ሁኔታ፣ ከሳሾች ይህንን አማራጭ ባለመቀበላቸው የደረሰባቸው ጉዳት ሊሰላ የሚገባው በቀረበው 24,500 ብር የካሬ ሜትር ዋጋ በሚሰላ ልዩነት መሰረት ነው በማለት በሰበር ሰሚ ችሎት ሲከራከር ቆይቷል።
ክሱን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት የወሰዱት ከሳሾች ቁጥር 103 ሲሆኑ የቀሩት ከሳሾች በግልግል ችሎቱ ውሳኔ በመስማማታቸው አፈጻጸም ተከፍቶላቸዋል።
ከካሳ ክፍያ (ብር 24,500.00) ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብራሪያና ክርክር እንዲቀርብ የሚያስችል ጭብጥ የተገኘበት በመሆኑ በ103 ከሳሾች እና በፍሊንትስቶንስ አ.ማ መካከል በተደጋጋሚ ቀጠሮ ተይዞለት በሰበር ሰሚ ችሎት ሲታይ ቆይቷል።
ከዓመታት ክርክር በኋላ፣ በትላንት ወዲያ የዋለው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱ ተከራካሪ ወገኖችን፣ የግልግል ውሳኔውን መሠረት ያደረጉ ሰነዶችንና ተያያዥ የሕግ ክርክሮችን ከመረመረ በኋላ፣ የግልግል ጉባኤውን ብይን ሙሉ በሙሉ አጽንቶታል።
በውሳኔው መሰረት ከሳሾች የጠየቁት የ99,000 ብር የካሬ ሜትር የካሳ መጠን ውድቅ የተደረገ ሲሆን ተገቢው የካሳ መጠን ሊሰላ የሚገባው ድርጅቱ ቤቶቹን ለማጠናቀቅ በጠየቀው የ24,500 ብር የካሬ ዋጋ ላይ ተመስርቶ መሆን እንዳለበት የተወሰነውን የስር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲጸና የተወሰነ መሆኑን ቲክቫህ ኢትዮጵያ በችሎቱ ተገኝቶ ሰምቷል።
በዚህም መሰረት ከሳሾች የከፈሉት ዋና ገንዘብ ከወለድ ጋር እንዲመለስላቸውና በዚሁ የዋጋ ልዩነት (24,500 ብር) አማካይ የካሬ ሜትር ዋጋ ብር 13ሺ 700 ብር በካሬ ተባዝቶ ካሳ እንዲከፈላቸው ብይን ተሰጥቷል።
በብይኑ መሰረትም ፍሊንት ስቶን ሆምስ ቤቶቹን አስረክባችኋለሁ ባለው ጊዜ ለደንበኞቹ ባለማስረከቡ ምክንያት ለ 103 ከሳሾች በአጠቃላይ 224 ሚሊየን 430 ሺ ብር ዋስትና ገንዘብ የሚከፍል ይሆናል።
ምንጭ: ቲክቫህ ኢትዮጵያ


















