በአዲስ አበባ ከተማ በህገ ወጥ መልኩ በመደራጀት የምናወርደው እና የምንጭነው እኛ ነን በሚል ግለሰቦችን ያስጨንቁ የነበሩ አልፎ አልፎም በግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ጫኝና አውራጆች ለመቆጣጠር የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከጫኝና አውራጅ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ላይ ጫና የፈጠሩ ስድስት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ እንደተቀጡም ተገልጿል።ካሳሁን አትክልት ፣ ይስማው አጋዝ፣ ስማቸው ጋሻው ፣ ጥላሁን አሰፋ ፣ ያረጋል ይርዳው እና ዮሱፍ ሙዜ የተባሉት ግለሰቦች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ግራር አካባቢ በጫኝና አውራጅ ስራ የተደራጀን ነን በማለት በተደጋጋሚ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማወካቸው የካራ ቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ስድሰቱን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እንዳጣራባቸው ታውቋል፡፡
ግለሰቦቹ የዋስትና መብት ተጠብቆላቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተው አራቱ ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ሳይቀርቡ ቢቀሩም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አፋጣኝ ችሎት ጥፋተኛነታቸውን በማረጋገጥ ሁለቱ በገንዘብ አራቱ ደግሞ በአራት ወር እስራት እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
የካራ ቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የዋስትና መብታቸውን ተጠቅመው በቀጠሮ ቀን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቀሩትን በሌሉበት እያንዳንዳቸው የአራት ወር እስራት የተፈረደባቸውን ካሳሁን አትክልት ፣ ይስማው አጋዝ፣ ስማቸው ጋሻው እና ጥላሁን አሰፋ ተከታትሎ በመያዝ ውሳኔው ተፈፃሚ እንዲሆንባቸው ለፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አስረክቧል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ ጫኝና አውራጅ ከማኅበረሰቡ አቅም በላይ ክፍያ በመጠየቅ የህብረተሰቡ የፀጥታ ሥጋት በመሆን ምሬት የሚፈጥሩ ከሆነ ህብረተሰቡ ለፖሊስ ሪፖርት የማድረግ ልምድ ሊኖረው እንደሚገባ እና ከሚመለከታቸው አካላት እውቅና አግኝተው በጫኝና አውራጅ ተደራጅተው እየሰሩ ያሉ አካላትም ህገ ወጥ ተግባራትን በመከላከል በኩል ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
ምንጭ፦ ፋስት መረጃ


















