በሪል እስቴት ግብይት ማስታወቂያዎች ይዘት ወስጥ ብዙውን ጊዜ ስሰማ እንደ መሃንዲስ የሚያሸማቅቀኝ በግብይት ባለሙያዎች በመቶኛ የሚነገሩ የግንባታ እርከን መግለጫዎች ይገኙበታል ( Percentage Progress)።
ገና ከመሬት ብቅ ያለን ህንጻ 50% የተጠናቀቀ ሲሉ፣ የመዋቅር (ስትራክቸር) ስራው ተጠናቆ ብሎኬት እየተደረደረለት ያለን ህንጻ 85% የተገባደደ፣ ገና ልስን እየተለሰነ ያለውን 90% የተጠናቀቀ…..ለመጠናቀቅ ሁለት ዓመት የሚጠብቀውን በሁለት ወር የሚረከቡት…. ምናምን ሲሉ ካለችኝ ከዚያችው ቁመት እየተሸማቀቅኩ ማለቄ ነውና ተሸማቅቄ ከመጥፋቴ በፊት የግንባታ እርከኖች ግምት ገላጭ የሆኑትን ላጋራ።
፩) 30% ደረሰ የሚባል ፕሮጀክት የመሰረትና ከመሬት በታች ያሉ ምድር ቤቶች (Basement) ስራ ተጠናቅቆ ከሬት በላይ የተወሰኑ ወለሎች የመዋቅር ስራ የተከናወነለት ሆኖ የህንጻውን ይዘት (ግዝፈት) በሚያሳይ ቁመና ላይ የደረሰ ነው።
፪) 60% አካባቢ ደረሰ ለመባል የመዋቅር ስራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ቢያንስ የብሎኬት ስራ የተጠናቀቀለት ሊሆን ይገባል።
፫) ከ70-85% ደረሰ ለማባል የውስጥና የውጭ ልስን ተጠናቆ፣ የቤቶች የውስጥ የኤሌክትሪክና የውሃ መስመር ዝርጋታዎች ተገባደው፣ የጋራ መጠቀሚያ ቦታዎች ደረጃና ኮሪደሮች የማጠናቀቂያ ስራዎች ተጠናቀው፣ የአሳንሰር ገጠማ ተጀምሮ፣ የውጭ ገጽታ ላይ የአሉሚኒየም መስኮቶችና በሮች ተጥመው፣ የውጭና የውስጥ የቀለም ስራ ቢያንስ ተጀምሮ ልንመለከት ይገባል።
፬) 90-95% ተጠናቀቀ ለመባል ብዙ የማጠናቀቂያ ስራዎች (Finishing Works) ተገባደው የመገልገያ ቁሶች (Fixtures) ገጠማ ማለትም የመብራት፣ ሶኬት፣ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫ፣ የመታጠቢያ ገንዳ፣ ኪችን ካቢኔት፣ የውስጥ በሮች፣ የውስጥ ቀለም ….. መጠናቀቅ አለባቸው።
፭) 95-100% ተጠናቋል ለመባል ዋና ዋና የሚባሉ ስራዎች ተጠናቀው በጠቅላላ በህንጻውና በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ያሉ ጉድለቶችን የማስተካከል የእርማት ስራዎች ውጪ ሁሉም ስራ የተጠናቀቀ ሊሆን ይገባዋል። እየተለዩ ከሚደረግ እርማትና ማስተካከያ ውጪ ሙሉ ስራው ሊጠናቀቀና የህንጻ የመጠቀሚያ ፈቃድ ሊያገኝ ይገባዋል።
ስለዚህ የሪል እስቴት አገበያይ ተቋማትና የሽያጭ ሰራተኞች ሆይ ፕሮጀክቶቻችሁ የደረሰበትን ደረጃ በትክክል የሚገልጽ መረጃ በመስጠት እኛንም ከመሳቀቅ ዘርፉንም ከውሸት ታደጉት።


















