የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ያደረገውን የንብረት ግብር መመሪያ ሕገ-ወጥ ነው በማለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ጥቅምት 7 ቀን 2018 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ሙሉ በሙሉ ሽሮታል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው፣ ክሱን የመሰረተው እናት ፓርቲ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት የማቅረብ የህግ መብትና ሥልጣን የለውም ሲል ብይን ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ተግባራዊ እንዲሆን ያወጣው የንብረት ግብር መመሪያ ነው። እናት ፓርቲ መመሪያው “ሕገ-ወጥ ነው” በማለት ክስ የመሰረተ ሲሆን፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ጥር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የፓርቲውን ክስ ተቀብሎ መመሪያው እንዲሻር ወስኖ ነበር።
በውሳኔው ቅር የተሰኘው የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማቅረቡ፣ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አፈጻጸም እንዲታገድ ተደርጎ ክርክሩ ሲካሄድ ቆይቷል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አምስተኛ ፍትሐብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ዛሬ በሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ፣ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተሳሳተ መሆኑን ገልጿል። ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው በምክንያትነት ያቀረባቸው ሶስት ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦
- ከሳሽ የሆነው እናት ፓርቲ ተከራይ እንጂ የቤትም ሆነ የቦታ ባለቤት ባለመሆኑ፣
- በጉዳዩ ላይ ፓርቲው በቀጥታ የሚነካው መብትም ሆነ ጥቅም ስለሌለው፣
- ፓርቲው ከሌላ አካል ክሱን እንዲያቀርብ የተሰጠው ውክልና ባለመኖሩ፣
ክሱን የማቅረብም ሆነ የመከራከር የህግ ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ የስር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲሻር ወስኗል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አክሎም፣ “የስር ፍርድ ቤቱ ክሱን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ተመስርቶ መዝጋት ሲገባው ወደ ክርክር ማስገባቱ ስህተት ነበር” ብሏል።
እናት ፓርቲ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ፍርድ ቤት የሄደው “በኑሮ ውድነት የጎበጠው ሕዝብ ላይ የተጫነውን ሕገ-ወጥ የብዝበዛ አዋጅ” ለማሻር እና “የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጋለጥ” መሆኑን ገልጿል። ፓርቲው፣ “በዚህ ጥረታችን አንዱን በከፊል፣ አንዱን ሙሉ በሙሉ አሳክተናል ብለን እናምናለን” ብሏል።
የፍርድ ሂደቱን እስከመጨረሻው እንደሚገፋበት የገለጸው እናት ፓርቲ፣ የፍርድ ቤቱን የውሳኔ ቅጂ እንደደረሰው ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግና ቀጣይ የይግባኝ ሂደቶችን ለህዝብ እያሳወቀ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ምንጭ፡ ዘ-ሐበሻ


















