የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት እንደገለጹት በአዲስ አበባ የነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ከአቅርቦቱ አንፃር በቂ አይደለም።
የቤት ፍላጎቱን ለማሟላትም ኮርፖሬሽኑ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው ከለውጡ በኋላ በተከናወኑ ተግባራት በ60 እና በ90 ቀናት በመንግሥትና የግል ባለሀብቶች ትብብር 35 ሺህ ቤቶች ተገንብተው በዝቅተኛ ኑሮ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በተለያዩ አማራጮች ከ445 ሺህ በላይ ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ተችሏል ነው ያሉት።
በ14 ዙሮች ከ350 ሺህ በላይ ቤቶች ለነዋሪዎች መተላለፋቸውን ገልጸው፤ ከፍላጎት አኳያ ሲታይ ግን በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ከ120 ሺህ በላይ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ለመገንባት ከአልሚዎች ጋር ውል በመዋዋል ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ያለበትን የፋይናንስ እጥረት ለመፍታት እና ተጨማሪ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ገንብቶ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በ4 ወራት ውስጥ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተገንብተው የተጠናቀቁ 3,146 የመኖሪያ ቤቶችን እና 306 የንግድ ቤቶችን በድምሩ 3,452 ቤቶችን በጨረታ አወዳድሮ በሽያጭ እንደሚያስተላልፍ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል፡፡
ከቤቶቹ ሽያጭ በሚገኘው ገንዘብ በአጠረ ጊዜ ቤቶችን በመገንባት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያስተላልፍ ሲሆን ሁሉንም የቤት አቅርቦት አማራጮች በማሳለጥ በቀጣዮቹ ጊዜያት የነዋሪዎቹን ችግር ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ገልፀዋል፡፡
ከለዉጡ ወዲህ በተደረገ ርብብር ተቋሙ ያለበትን እዳ ለማቃለል ባደረገው ጥረት 36 ቢሊየን ብር የመለሰ ቢሆንም አሁንም 37.7 ቢሊየን ብር እዳ እንዳለበት እና ይህ በየጊዜው እየጨመረ ከሚመጣው ወለድ ጋር ተያይዞ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ኃላፊው ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ የሚታየውን የቤት እጥረት ለመፍታት በርካታ ጥረት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው እስከአሁን በተደረገው ጥረት በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ የተደረገ ቢሆንም የባንክ የቦንድ ብድር እጥረት የቤት አቅርቦቱን ከነዋሪው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ማረግ እንዳልተቻለም ገልፀዋል።
በአጠቃላይ ሁሉንም አይነት አማራጮች በመጠቀም የቤት አቅርቦቱን ለማስፋት ከፍተኛ ርብርብ እንደማደረግ ኃላፊው በመግለጫቸው ገልፀዋል
ማስታውሻ፦
ማንኛውም ለጨረታ የቀረቡ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን ለመግዛት የሚፈልግ ሁሉ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ በመያዝ የጨረታ ሰነድ ከ27/05/2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 20/06/2016 ዓ.ም ድረስ ቅዳሜን እስከ 11፡00 ሰአት እና እሁድ ግማሽ ቀን ጨምሮ ዘወትር በስራ ቀናት ከጠዋቱ 1፡30 እስከ ማታ 1፡30 ድረስ በመቅረብ የማይመለስ ብር 1000.00(አንድ ሺህ) በመክፈል የጨረታ ሰነዱ መግዛት የሚቻል መሆኑ የተገልፀ ሲሆን የሰነድ መሸጫ ቦታ ከዚህ በሰንጠረዡ ተመላክቷል።

Source: Official Telegram page (AA Housing Development Corporation)


















