የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የ1ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ አሸናፊዎችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
በቢሮው የለማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ፣ በከተማዋ ላለፉት አምስት ዓመታት ቆሞ የነበረውን መሬትን በሊዝ ጨረታ የማስተላለፍ ተግባር ዳግም መጀመሩን አስታውሰው፣ ከግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በይፋ ተከፍቶ አሸናፊዎቹ የተለየው የ1ኛው ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ አሸናፊዎች ስም ዝርዝር ይፋ መደረጉን ነግረውናል፡፡
በዚህ ጨረታ ዝቅተኛ ዋጋ የተመዘገበው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሲሆን፣ ይህም በካሬ ሜትር 20 ሺህ ብር ነው፡፡ ከፍተኛው በአራዳ ክፍለ ከተማ መሆኑን ጠቁመው፣ በካሬ ሜትር 414 ሺህ ብር እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ለ21 ሺህ 636 ተጫራቾች የጨረታ ሰነድ መሸጡን ጠቅሰው፣ ከእነዚህ ውስጥ 11 ሺህ 457 ሰነዶች ተሞልተው ሳጥን ውስጥ ገብተዋል ብለዋል፡፡
የሊዝ ጨረታው ቆሞ በመቆየቱ መሬትን በግዢ ማግኘት የማይችሉ የከተማዋ ነዋሪዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ከመሆን ርቀዋል የሚሉት አቶ ሀብታሙ ይህኛው ጨረታ ሁሉን አሳታፊ እንዲሆን ታስቦ መውጣቱን ገልፀዋል፡፡
ቀደም በነበሩት ጊዜያት መሬት በምደባና በጨረታም ጭምር ለተጠቃሚዎች ይተላለፍ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ፣ ይሁን እንጂ ባለፉት ሥርዓቶች የመሬት አስተዳደር ክፍተት የነበረበት በመሆኑ ብልሽቱን ለማስተካከል የተለያዩ የኦዲትና ክትትል ሥራዎች ሲደረጉ መቆየቱ ክፍተቱን አጥርቶታል ብለዋል፡፡ የመሬት አስተዳደርና የአስተላለፍ ስርዓቱን ለማጥራት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የሊዝ ጨረታውን ማስተናገድ ባለመቻሉ ተቋርጦ መቆየቱን አክለው ገልፀዋል፡፡
የነበሩ ክፍተቶች በከፊል ተጣርተው መስተካከላቸውን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ ከማጣራቱና ከማስተካከሉ ጎን ለጎንም ይህን ጨረታ ማውጣቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የበፊቱን ብልሹ አሰራሮች የቀረፈ ሆኖ ሊወጣ ችሏል፡፡
ጨረታው ግልፅነት የተሞላበት፣ አቅም አለኝ የሚል ሁሉ ተሳትፎ ያደረገበት ሆኗል ብለዋል፡፡ ለተጠቃሚዎች በማስተላለፍ ሂደት ውስጥ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
1ኛ ዙር የመሬት ሊዝ ጨረታ ማስታወቂያ በወጣበት ወቅት አቶ ሀብታሙ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ በገለፁት መሠረት፣ ቢሮው በሊዝ ጨረታ ለማስተላለፍ ያዘጋጃቸው መሬት 297 ፕሎት ሲሆን፣ በሄክታር ሲሰላ 14 ነጥብ 3 የሚሆን ነው፡፡
ለጨረታ የቀረበው መሬት በአስራ አንድ ክፍለ ከተሞች የሚገኝ ሲሆን፣ በከተማ ደረጃ የተጠና የመሬት አጠቃቀም መነሻ ዋጋን መሰረት በማድረግ የቀረበ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት መሬትን በሊዝ ጨረታ ማስተላለፍ እንዲቆም ቢደረግም፣ ለተለያዩ መንግስታዊ፣ መንግስታዊ ያልሆኑና የግል ተቋማትን ጨምሮ በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔና የሚመለከታቸው የመሬት አስተዳደር ተቋማት ውሳኔ መሬት በምደባ ሲተላለፍ እንደነበር አቶ ሀብታሙ ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲባል በተለያየ ጊዜ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ እግድ ሲጣል ቆይቷል፡፡ መሬትን በሊዝ ጨረታ ማስተላለፍ እንዲቆም የተደረገው ከዚህ ቀደም የነበሩትን የአሰራር ችግሮች ለማረም ታስቦ እንደሆነ አቶ ሀብታሙ አስረድተዋል፡፡
አልሚዎች ተጫርተው አሸናፊ ከሆኑ በኋላ መሬቱን ለማስረከብ የሚተላለፉ የተለያዩ ቦታዎች ላይ “የይገባኛል” ጥያቄዎች ይነሱባቸው ነበር፡፡ አሁን ለመተላለፍ የተዘጋጁ ቦታዎች ወደ መሬት ባንክ የገቡና ከይገባኛል ጥያቄ ነፃ መሆናቸውን የተጣራ እንደሆኑም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡
ለጨረታ ከሚቀርቡ ቦታዎች መካከልም ከዚህ ቀደም በምደባና ጨረታ ወስደው ያላለሙና እርምጃ የተወሰደባቸው፣ በተለያየ ጊዜ በህገ ወጥ መንገድ የተወረሩና ወደ መሬት ባንክ የገቡ መሬቶች ይገኙባቸዋል፡፡
በሊዝ መሬትን ጨረታ ማስተላለፉ ዓላማው ህዝቡን ተጠቃሚና የከተማ አስተዳደሩም ገቢ ማሳደግ እንደሆነ ያነሱት አቶ ሀብታሙ፣ ቀጣይም ህዝቡንና ከተማዋን ተጠቃሚ ለማድረግ መሬትን በሊዝ የማስተላለፍ ስራው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
ምንጭ፡ አዲስ ልሳን ጋዜጣ


















