በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ እና የግንባታ ግብዓት አቅራቢዎችን ከገዢዎችና ከተቋራጮች ጋር በቀላሉ ለማገናኘት የተዘጋጀው ኢቫኮኔት (EvaConnect – Eva Construction Network Market) ፕላትፎርም በይፋ ተመርቋል።
ሐምሌ 18 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለገሃር በሚገኘው አመልድ ህንፃ በተካሄደው የዚሁ የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኮንስትራክሽን ተቋራጮች፣ የምህንድስና አማካሪዎች፣ የግብአት አቅራቢዎችና አስመጪዎች፣ አልሚዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በኢንጂነር አቤሴሎም መለሰ የተመሰረተው ይህ የኮንስትራክሽን ዲጂታል ፕላትፎርም የግንባታ እቃዎችን ዋጋ፣ የማሽነሪዎችን የክራይ ተመን፣ የወቅታዊ ዋጋ ንፅፅር፣ እንዲሁም የባለሙያዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ትስስርን ለማድረግ የሚያገለግል ዲጂታል ፕላትፎርም (Online Marketplace) ነው።
ፕሮግራሙን በይፋ ያስጀመሩት የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት “የEvaconet ዲጂታል የኮንስትራክሽን ገበያ ‘የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ’ን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት የሚያግዝ እንዲሁም የዘርፉን ባለድርሻዎች በአንድ ቋት በማስተሳስር በኮንስትራክሽን የገበያ ሰንሰለት ውስጥ ግልፀኝነትን በማስፈን የዘርፉን ተዋንያን ለጤናማ የገበያ ውድድር የሚጋብዝ” መሆኑን በአፅንኦት ጠቁመዋል።

በEvaconet ዲጂታል የኮንስትራክሽን ገበያ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በከፍተኛ የዩኒቨርስቲ ተቋማት እንዲሁም በተናጠልም በተማሪዎች መካከል የኮንስትራክሽን ዲዛይን የፈጠራ ውድድር የተከናወነ ሲሆን ከፍተኛ ሙአለ-ንዋይ የሚፈስበትና በርካታ የሰው ኃይልን አሰባጥሮ በማቀፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአዎንታዊ የእድገት እምርታና ምዕራፍ ላይ የሚገኘው የሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዳስትሪ በመሰል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች መታገዙ እንደሀገር ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳና ጠቀሜታ የሚያስገነዝብ በምሁራኖች የተመራ የጋራ ውይይትንም አስተናግዷል።
በዚሁ የEvaconet ዲጂታል የኮንስትራክሽን ገበያ ምርቃት “ሕይወትን በኮንስትራክሽን እንገባ” በሚል መሪ-ቃል በአቢሲኒያ የስነ-ጥበባትና ሞዲሊግ አካዳሚ አስፈፃሚነት እየተመራ የቀረበው የኮንስትራክሽን ሞዴሎች ትዕይንት በዓይነቱ የተለየና በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሞያዎችንና አጋዥ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከውበት ባሻገር እንድንመለከት የጋበዘ ማራኪ ትዕይንት ከመሆኑም በላይ በሀገራችን የመንገድ ስራዎች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት የ97 ዓመቱ አዛውንት አቶ ዘውዴ ላእከማርያም እድሜ ሳይገዳቸው በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው አባታዊ ምርቃት ያስተላለፉ ሲሆን ቀሪ ፕሮግራሙም በአዝናኝ ሙዚቃና በውብ ባህላዊ ጭፈራዎች ታጅቦ ባለቀለት ድምቀት የተከናወነ ነበር።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ለዝግጅቱ መሳካት ጉልህ ሚና የነበራቸው የከተማና መሰረተ-ልማት ሚ|ር፣ ኢንጂኒየር ቤጃይ ናይከርና ተቋማቸው እንዲሁም ወ|ሮ ፍሬዓለም ሽባባው በግል ልዩ ስጦታዎች የተበረከተላቸው ሲሆን በተቋም ደረጃ ዝግጅቱን ለደገፉ ኮንትራክተሮች፣ በሒደቱ ለተሳተፉ የዩኒቨርሲቲ ተቋማትና ተማሪዎች ብሎም በግለሰብ ደረጃ አዎንታዊ አበርክትዎ ለነበራቸው ግለሰቦችና ባለሞያዎችም የተሳትፎ፣ የምስጋና እና የእውቅና ሰርቲፊኬት በማበርከት፤ ከዘርፉ ተጠሪና ባለድርሻ አካላት ባለፍ በርካታ የዩኒቨርስቲ ተቋማትንና ተማሪዎችን በማሳታፍ በየዓመቱ እንደሚከናወን ከወዲሁ እቅድ የተያዘለት የEvaconet ዲጂታል የኮንስትራክሽን ዲዛይን የፈጠራ ውድድር እና በዓለ ምረቃው በጋለ የአብሮነት ድባብ እንደደመቀ በዕለቱ አመሻሽ ተጠናቋል።
ፕላትፎርሙ ለምዝገባ ክፍት ሲሆን፣ በዘርፉ ያላችሁ ባለሙያዎችና ድርጅቶች www.evaconet.com በመጎብኘት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻልም ተገልጿል።
ምንጭ: ምታቸው፣ ቤተኛ ሚዲያ

















