የኢትዮጵያ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ዘመናዊ የመኖሪያ እና የንግድ ተቋማት ግንባታን ለመጀመር የሚያስችሉትን ሁሉንም አስፈላጊ ቅድመ-ዝግጅቶች ማጠናቀቁንና ወደ ተግባር ለመግባት መዘጋጀቱን አስታወቀ።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ወደ ትግበራ ምዕራፍ የተሸጋገረው ባለፈዉ ቅዳሜ ዕለት በጁባ ከተማ በተፈረመው የመጨረሻ የኦፕሬሽን ውል መሠረት ሲሆን፣ ስምምነቱ ቀደም ሲል በሁለቱ ወገኖች መካከል በአዲስ አበባ ተፈርሞ የነበረውን የመግባቢያ ሰነድ በቀጥታ ወደ ሥራ የሚያስገባ ነው።
ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል እና የደቡብ ሱዳን የመካከለኛው ኢኳቶሪያ ግዛት ገዥ ኢማኑኤል አዲል በጋራ ፈርመውታል።
በዚህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሠረት ኮርፖሬሽኑ በጁባ ከተማ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ ዘመናዊ የንግድ ማዕከላትን እና የመኖሪያ ሕንፃዎችን ግንባታ በበላይነት ይመራል ተብሏል።
ምንጭ: capital


















