በ450 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለሚገነባው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሰራተኞች ሁለተኛ ምዕራፍ የ5 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ 5,000 ቤቶችን ለማልማት ኦቪዲ ግሩፕ ከተሰኘው የአገር ውስጥ የግንባታ ድርጅት ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ባለፈው ሳምንት ተፈራርሟል።
ኦቪድ ግሩፕ 5 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሸጥ የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ
የግንባታ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋዩን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስቀምጠዋል። አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ የመኖሪያ ቤት የማግኘት ፍላጎት የመዲናዋ ነዋሪዎች የመጀመሪያ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

የመዲናዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ምላሽ ለመስጠትም አልሚዎችን ማሳተፍ የሚያስችል በሕግና ፖሊሲ የተደገፈ አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የመንግሥትና የግል አጋርነትና የግል ቤት አልሚዎች በራሳቸው መንገድ ማልማት የሚችሉበት ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሠራተኞቻቸው የመኖሪያ ቤት መገንባት ለሚችሉ ተቋማትም መሬት በማቅረብ መገንባትና ማስገንባት እንዲችሉ እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በግንባታ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ሳሙኤል ታፈሰ፣ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታረቀኝ ገመቹና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

በ17 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የቤቶቹ ግንባታ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ ልዩ ሥሙ ሃያት-49 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ግንባታው በሰንሻይን ኮንስትራክሽንና በቻይናው ኮንስትራክሽን ኮሙኒኬሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ) የሚከናወን ሲሆን በአራት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።
በፕሮጀክቱ ከ5 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚይዝ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ፣ የልጆች መጫወቻ፣ አረንጓዴ ሥፍራ፣ ትምህርት ቤት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራና የገበያ ማዕከላት እንደሚይዝ ተጠቁሟል።

እንዲሁም ሰንሻይን ኮንስትራክሽን አክሲዮን ማሕበር፣ መንግስት ከስድስት ዓመታት በፊት በነጻ ባስረከበው 3.8 ሄክታር መሬት ላይ ያስገነባቸውን 5ሺህ ቤቶች መርቀዋል።

















