የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ፣ የከተማው መምህራን ማህበር እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ስራ ኮሚሽን ጉዳዩን አስመልክቶ በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በጋዜጣዊ መግለጫው እንዳስታወቁት ከተማ አስተዳደሩ መምህራን የቤት ባለቤት ሆነው ከተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ተላቀው ትውልድ የመገንባት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው ከዚሁ ጋር በተገናኘ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ከ30ሺ በላይ ቤት ፈላጊ መምህራን መረጃ መደራጀቱን አስታውቀዋል።

ዶክተር ዘላለም አክለውም ቤት ፈላጊዎቹን ቅድመ ሁኔታ አሙዋልተው ወደ መደረጃጀት እንዲገቡ ከቢሮ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርትና የህብረት ስራ ኮሚሽን መዋቅሮች ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው መምህራን የማደራጂያ ደንብና መመሪያ በሚፈቅደው መሰረት የቁጠባ ባህላቸውን አሳድገው ወደ ግንባታ መግባት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በተለይም ክብርት ከንቲባና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ መምህራን በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው መምህራኖችም የመኖሪያ ቤት ሁለተኛ የስራ ቦታቸው እንደመሆኑ በአግባቡ በመቆጠብ የቤት ባለቤት የሚያደርጋቸውን ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

















