ቅጠል ተራን ወደ ንፁህ አረንጓዴ ለዜጎች ክብር የሚመጥን መኖሪያ ስፍራ ተቀይሯል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
960 ቤቶችን በአራት ወር ዉስጥ ገነብተን ከቦታው ላይ ለተነሱ ነዋሪዎች አስተላልፈናልም ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለፁት ቅጠል ተራ ለመኖር እጅግ ምቹ ያልነበረ፤ ለሰው ልጅ ክብር የማይመጥን፤ እጅግ የቆሸሸ፣ የተፋፈገ እና የተጨናነቀ በመሆኑ የሰው ህይወትም በአስከፊ ሁኔታ በእሳት አደጋ ያጣንበት አካባቢ ነበር።
ዛሬ ግን እጅግ ያማሩ፥ ዘመናዊና ሁሉንም ነገር የተሟሉላቸው ባለ 9 ወለል የሆኑ ብዛታቸው 9 ህንጻዎችን 960 ቤቶች ተገንብተው ወደ ምቹ መኖሪያ አካባቢ ተቀይሯል።
“የመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር “በ11, 000 ካሬ ሜትር ላይ የተገነቡ G+8 የሆኑ ዘጠኝ (9 )ብሎኮች በአጠቃላይ 960 ቤቶች ያሉት ሲሆኑ፣ ሰፊ የስራ እድልን የሚፈጥሩ 371 የንግድ ሱቆች በውስጡም የህጻናት የመጫወቻ ስፍራ፣ የስፓርት ማዘውተሪያ( የኳስ ሜዳ፣ ቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የመረብ ኳስ፥ የሰውነት ማጎልመሻ ቦታዎች) ፥ ለነዋሪዎች የመኪና ማቆምያ ፓርኪንግ፥ ለኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፥ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ፥ዘጠኙም ብሎኮች ላይ የጋራ መጠቀሚያ ሰገነት፥ ሊፍት፥ የፍሳሽና የኤሌክትሪክ መስመሮች በዘመናዊ መልክ ተሟልተው ተገንብተዋል።
በመርካቶ የበጎነት የመኖሪያ መንደር የሰው ህይወትን የሚቀይር ፥ መርካቶ አካባቢን “ተራ” በሚል ስያሜ የተሰጣቸው ( ቅጠል ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ገብስ ተራ፣ ሳር ተራ፣ ቦንብ ተራ … ወዘተ) ጎስቋላ አካባቢዎችን ወደ ውብ አካባቢ የመለወጥ ጉልህ ማሳያ ነው።
ቃል በተግባር ማለት ይህ ነው፥ እንደዚህ ዓይነት የተወሳሰበ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ለሰው ልጆች የሚመጥኑ፥ ነዋሪዎች የክብር ኑሮ እንዲኖሩ፥ ህይወታቸውን የሚቀይሩ ተግባራትን ያለ እረፍት 24/7 በመፈፀም ነዋሪዎች አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ ማድረግ ነው።
የስራዎቻችንን ማዕከል ሁሉ ሰው ተኮር አድርገን፥ ከተማችን ውብ ፅዱ፥ ለነዋሪዎቻችን የተመቸች ከተማ እንድትሆን ያለ እረፍት የመስራት ተግባራችን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን።
ካላችሁ አካፍላችሁ ከከተማ አስተዳደራችን ጎን በመሆን የበጎ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ፥ ዛሬም በቅጠል ተራ የበጎነት መንደር እንድንቀይር ያገዛችሁን በተለይ ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ፥ በግንባታው የተሳተፋችሁ ሁሉ በነዋሪዎች ስም ከልብ እናመሰግናለን ሲሉ ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ጋዜጣ ፕላስ


















