ይህ ከላይ በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ኢዩኤል(አቢቲ) በጎንደር ዩኒቨርስቲ የኪነህንፃ (Architecture) 5ኛ ዓመት ተማሪ ነበር።
ኢዩኤል ታዬወርቅ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ኬንያ ኢምባሲ ከፍ ብሎ ልደታ ቤተክርስቲያን አካባቢ ነው።
የፋሲካ በዓልን አያቱ ጋር አክብሮና እዛው ሲጫወት አድሮ በማግስቱ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ከመጣ ታናሽ ወንድሙ ጋር ወደ ቤተሰቦቹ ቤት ሲመለስ ኬንያ ኢምባሲ አካባቢ እየተሰራ ከሚገኝና 14 ፎቅ እርዝመት ካለው ፎቅ ላይ ተወርውሮ የወረደ ብረት ጭንቅላቱ ላይ መቶት በአበባነት እድሜው በአሳዛኝ ሁኔታ ተቀጥፏል።
ከጥቂት ወራት በኋላ የበኩር ልጃቸውን ለማስመረቅ በተስፋ የሚጠባበቁ ወላጆችን በህንፃ ገንቢዎች ንዝህላልነት በድንገት ያውም በአሰቃቂ ሁኔታ ፍቅራቸውን ስስታቸውን ሲነጠቁ በምን ቃል ምን ብሎ ማፅናናት ይቻላል?
ይህ አሰቃቂ ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር አብሮት በነበረውና ሁሉን ነገር ባየው ወንድሙ ላይ በቀሪው ህይወቱ ለሚፈጠረው ስነልቦናዊ ጫናና ትራውማስ ማካካሻው ምንድነው?
ሁላችንም አዝነነናል ፣ ልባችን ተሰብሯል። ነገር ግን የወላጆቹን ልክ የሌለው ሀዘን ማየት ከልብ የማይወጣ ሌላ ከባድ ህመም ነው።
በህንፃ ግንባታ ወቅት አስፈላጊውን የስራ ላይ ደኅንነት (safety) ማሟላትን ግዴታ ለማድረግ የስንት ሰው ህይወት ማለፍ አለበት? የስንት ወላጅና ቤተሰብ ልብስ መሰበር አለበት?
እዚህ አገር በህግ የተደነገገ እንኳን ቢሆን ክትትልና ቅጣት ከሌለ የሚተገብር ስለሌለ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጥብቅ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር ቢያደርጉ የግንባታ ባለሙያዎችንም ሆነ ተላላፊ መንገደኞችን ካልታሰበ የሞት አደጋ መታደግ ይቻላልና Safety first ለሚለው መርህ ትኩረት ቢሰጥ እላለሁ።
ሰኔ 1 ቀን 1992 ዓ.ም የተወለደው ኢዩኤል ታዬወርቅ ሚያዚያ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በ24 አመቱ ህይወቱ አልፎ ትላንት ሚያዚያ 30/2016 ዓ.ም ከራሺያ ኢምባሲ ጀርባ በምትገኘው ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት ስርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል።
ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ለወላጆቹ ፣ ለቤተሰቦቹ ፣ ለዘመድ አዝማዱ ሁሉ የመፅናኛውን ቃል ወደ ልባቸው ይላክልን።
ምንጭ። Dawit Taye


















