ቤት እንዴት ይኑረን? የብዙሃን ጥያቄ ነው።
ቤት እንዴት ለዜጎች ላዳርስ? የመንግስት ጥያቄ ነው።
ቤት ገንብቼ ሸጬ ወይም አከራይቼ እንዴት ገንዘብ ላግኝ? የብዙ አልሚዎች ጥያቄ ነው።
ሁሉም ጥያቄዎች ለሁሉም ጠያቂ አካላት ከባድ የሆኑት በሀገራችን በኢትዮጵያ ነው።
እና የቤት ጉዳያችን እንዴት መላ ይኑረው? መልሱ ከጥያቄዎቹ ውስጥ የሚወጣ ነው።
መጀመሪያ ቤት ይኑረኝ የሚል መግዣ ወይም መከራያ አቅሙን ያዳብር። ቀጣዩ የአባትየው የመንግስት ነው።
ለዜጎች እንዴት ቤት ላድርስ የሚለው መንግስትም ቸርነቱን የሚከተሉትን በማድረግ በተግባር ያሳይ:-
፩)ዜጋው ቤት መግዣ አቅም እንዲያገኝ ገቢው እንዲያድግ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠርበትን አቅጣጫ ቀይሶ ይተግብር። እየወጡ ያሉ በርካታ ፖሊሲዎች ይህንን ታሳቢ አድርገው ነው ብለን ከተሟላ ሰላም ጋር ትግበራውን በተስፋ እንጠብቅ።
፪)በአነስተኛ ክፍያ ለዜጎች ቤት ገንብቶ ለማስተላለፍ የሚሆን መሰረተ ልማት የተሟላለት መሬት ከክፍያ ነጻ ለአልሚዎች ያቅርብ።
፫) በቁርጥ ዋጋ በአነስተኛ ወጪ ቤቶች ገንብተው ለሚያስተላለፉ አልሚዎች ከረጥ ነጻ የግንባታ ግብዓቶች እንዲያገቡ መፍቀድና በትክክል ለተባለው ግንባታ መዋሉን መከታተል።
፬) ለመጀመሪያ ቤት ገዢዎች ድጋፍና ማበረታቻ እንዲሆን በግብይት ውስጥ የሚከፈለውን 15% VAT 4% አሹራና 2% የቴምብር ቀረጥ በጠቅላላው 21% ክፍያን ማስቀረት።
፭) ከላይ የተጠቀሱት ሁሉ ቢደረጉም በሀገራችን ያለው የቤት ዋጋና የቤተሰብ ገቢ ስሌት እንደሚያሳየው ብዙዎች ቤት ለመግዛት የሚሆን አቅም የላቸውምና በረጅም ጊዜ ክፍያ ቤት እንዲያገኙ የሚያደርግ በተራዘመ ክፍያ በአነስተኛ ወይም ከወለድ ነጻ የባንክ ብድር ማመቻቸት።
፮) ፈቃደኛ አልሚዎችና በተለያዩ ግንባታና የግንባታ እቃ ማምረት ስራ የተሰማሩ ባለሀብቶች በተሰላና በተረጋገጠ ትርፍ በቁርጥ ዋጋ ቤቶችን እየገነቡ እንዲያስተላልፉ ቢደረግ።
ከላይ የተዘረዘሩትን የተመለከተ አንባቢና ሀሳቡን የተስማማበት አሁን ባለንበት ሁኔታ የመንግስት ቸርነትና ችሮታና ልዩ ትኩረት ዜጎች ቤት እንዲኖራቸው ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ይረዳል። መንግስትን ቀረብ የሚለው ካለም ይህንን ቢያደርግና አባትነቱን እንዲያሳይ ይመክራል ያስመክራል።
ይሄ መሰረታዊ ችግራችን ስር ነቀል መፍትሄ ይፈልጋል የምትሉ እስኪ ስር ነቀል ሀሳቦች ለግሱ። መንግስት መር የቤት አብዮት ያስፈልገናል።


















