ሀቢታት ፎር ሂዩማኒቲ ኢትዮጵያ የተባለው ግብረ-ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት ሲሰራ በቆየው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ዙሪያ እና ስለ ኢትዮጵያ የቤት ፖሊሲ ትናንት ምሽት በሃይሌ ግራንድ ሆቴል ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ላይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ሄለን ደበበ ተገኝተው፣ መንግስት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረው መንግስትም ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመኖሪያ ቤት ግንባታን ለማፋጠን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም ደግሞ ከግል አልሚዎች ጋር የሚደረገው ትብብር ተስፋ ሰጪ እንደሆነም አክለዋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም፣ ከሀቢታት ፎር ሂዩማኒቲ ጋር የተደረገው ውይይት ከግል አልሚዎች ጋር የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ የሀቢታት ፎር ሂዩማኒቲ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ጆናታን ሮክፎርድ፣ ድርጅታቸው በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ በመኖሪያ ቤት ልማት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ በመግለጽ፣ መንግስት እያቀረባቸው ያሉት የመኖሪያ ቤት አማራጮች ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ገልፀዋል።
ሀቢታት ፎር ሂዩማኒቲ በ1993 ዓ.ም (እ.ኤ.አ.) በአሜሪካ የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ70 በላይ በሆኑ ሀገራት ውስጥ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ በማገዝ ላይ ይገኛል።
ምንጭ፡ ጌጡ ተመስገን


















