እንደ አንድ በጉዳዩ የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጽሁፉን እንደሰራ ዜጋ ገርበብ ብሎ የተከፈተው የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት መብት የሚሰጠው መመሪያ በዚህ ሳምንት በስራ ላይ መዋሉን ተከትሎ በውስጡ ከያዛቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ወሳኞቹን ነቅሼ ከተወሰኑ ሀገራት መመሪያዎች ጋር አነጻጽሬ በሚከተለው መልክ አቅርቤዋለሁ።
ይህ ሰነድ በከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር የወጣው መመሪያ ቁጥር 1147/2018 ሲሆን፤ የውጭ ሀገር ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ዝርዝር የህግ አሰራር እና መመሪያዎችን ያስቀምጣል።
ይህ መመሪያ የሀገሪቱን የሪል እስቴት ዘርፍ ለማነቃቃት እና የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ ታስቦ የወጣ ነው።
ሀ) ዋና ዋና መስፈርቶች
ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ ቤት ለመግዛት ወይም ለመስራት ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ማግኘት አለበት።
የሚከተሉትንም ማሟላት ይጠበቅበታል፡-
- የጉዞ ሰነዶች፦ የፀና ፓስፖርት፣ የመግቢያ ቪዛ ወይም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ።
- የወንጀል ታሪክ፦ ከሚኖርበት ሀገር የተሰጠ ከወንጀል ነጻ የመሆን ማረጋገጫ ማስረጃ።
- የገንዘብ ማስረጃ፦ ለቤቱ የሚያስፈልገውን አነስተኛ የገንዘብ መጠን በባንክ ገቢ ማድረጉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ።
- የሰላምና ደህንነት ማረጋገጫ፦ ከሀገር ሰላም፣ ደህንነት፣ ፀጥታና ከህዝብ ሞራል ጋር የተያያዘ ክልከላ የሌለበት መሆን።
ለ) ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን እና የቤት ብዛት ገደብ:-
ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ ሊኖረው የሚችለው ከፍተኛው የቤት ብዛት አንድ (1) ብቻ ነው። ለመኖሪያ ቤት ባለቤትነት የሚያስፈልገው አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ መጠን እንደየአካባቢው ይለያያል፦
- 150,000 ዶላር፦ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሸገር ከተማ።
- 120,000 ዶላር፦ በድሬዳዋ አስተዳደር ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣በሲዳማ እና በሌሎች ዋና ዋና ክልሎች። ( ሸገርና ኦሮሚያን የተለያየ መስፈርት ያስቀምጣል)
- 100,000 ዶላር፦ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች።
ሐ) ከሌሎች ሀገራት ህጎች ጋር ማነጻጸሪያ (Comparative Analysis)
የኢትዮጵያን አዲሱን መመሪያ ከዓለም አቀፍ የሪል እስቴት ገበያዎች (ዱባይ፣ ቱርክ፣ ደቡብ አፍሪካ) እና ከጎረቤት ሀገራት (ኬንያ፣ ሩዋንዳ) ጋር ስናነጻጽረው የሚከተሉትን ህጎች እናገኛለን፦
፩) የመሬት ባለቤትነት (Land Tenure)፦
◦ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ፦ የውጭ ዜጎች ህንጻውን/ቤቱን ብቻ ነው በባለቤትነት መያዝ የሚችሉት፤ መሬቱ ግን የመንግስት ሆኖ በሊዝ (Leasehold) መብት ነው የሚተዳደረው። የኬኒያ በተለየ ሁኔታ ህንጻውንም በሊዝ ነው የሚያስተዳድረው)
◦ ዱባይ (UAE)፦ በልዩ ሁኔታ በተፈቀዱ ቀጠናዎች (Designated Freehold Areas) ውስጥ የውጭ ዜጎች መሬቱንም ሆነ ቤቱን 100% በቋሚነት (Freehold) ሙሉ በሙሉ መግዛት ይችላሉ።
◦ ደቡብ አፍሪካ፦ ለውጭ ዜጎች እጅግ ክፍት የሆነ ህግ አላት፤ ማንኛውም የውጭ ዜጋ በአፓርትመንትም ሆነ በከተማ መሬት ላይ ሙሉ የቋሚ (Freehold) ባለቤትነት መብት አለው
፪) የመግቢያ የገንዘብ ገደብ (Minimum Investment Threshold)፦
◦ ኢትዮጵያ፦ የ150,000 የእሜሪካን ዶላር ዝቅተኛ የዋጋ ገደብ (በአዲስ አበባ) በማስቀመጥ የውጭ ዜጎች ግዥ በከፍተኛው የገበያ ደረጃ ላይ እንዲገደብ አድርጋለች።
◦ ዱባይ (UAE)፦ ቤት ለመግዛት ምንም ዓይነት ዝቅተኛ የዋጋ ገደብ የለም። ነገር ግን የ2 ዓመት ነዋሪነት ቪዛ ለማግኘት ቢያንስ የ 750,000 AED (ወደ 204,000 ዶላር) ንብረት መግዛት ያስፈልጋል። የ10 ዓመት ወርቃማ ቪዛ (Golden Visa) ለማግኘት ደግሞ ቢያንስ 2 ሚሊዮን AED (544,000 ዶላር) ንብረት መግዛት ይጠይቃል።
◦ ቱርክ፦ የውጭ ዜጎች ለማንኛውም ዋጋ ቤት መግዛት ይችላሉ፤ ነገር ግን በሪል እስቴት ኢንቨስትመንት የቱርክን ዜግነት (Citizenship by Investment) በቀጥታ ለማግኘት ቢያንስ የ400,000 ዶላር ንብረት መግዛት እና ንብረቱን ለ3 ዓመታት አለመሸጥ ግዴታ ያስቀምጣሉ።
◦ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ፦ የውጭ ዜጎች ንብረት ለመግዛት የሚጠየቁበት ምንም ዓይነት ዝቅተኛ የዶላር የዋጋ ገደብ የለም፤ እንደየአካባቢው የገበያ ዋጋ በነጻነት መግዛት ይችላሉ።
፫) የቤት ብዛት ገደብ (Property Quantity)፦
◦ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ፦ የውጭ ዜጋን በግል ስሙ በአንድ (1) የመኖሪያ ቤት ብቻ ይገድባሉ።
◦ ዱባይ፣ ቱርክ እና ደቡብ አፍሪካ፦ የውጭ ዜጎች የገንዘብ አቅማቸው እስከፈቀደ ድረስ ምንም ዓይነት የቤት ብዛት ገደብ ሳይደረግባቸው በርካታ ቤቶችን እና አፓርትመንቶችን መግዛት፣ ማከራየት እንዲሁም መልሰው መሸጥ ይችላሉ።
መ) የፈቃድ ቆይታ እና ምዝገባ
- የአንድ ዓመት ገደብ፦ የሚሰጠው ፈቃድ የሚያገለግለው ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ለአንድ ዓመት ብቻ ነው።
- ማራዘሚያ፦ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ቤት መግዛት ካልተቻለ ተጨማሪ የ1 ዓመት ማራዘሚያ ሊሰጥ ይችላል።
- የገንዘብ መመለስ፦ ፈቃዱ ተራዝሞለት ግዥ ካልፈጸመ፣ በዝግ የባንክ ሂሳብ የተቀመጠው ገንዘብ ይመለስለታል።
- ባለቤትነትን ማስመዝገብ፦ ቤት ከገዛበት ቀን ጀምሮ በ30 የስራ ቀናት ውስጥ ለሚኒስቴሩ ማሳወቅ አለበት。
ሠ) ክልከላዎች እና በባለቤትነት ሊያዙ የማይችሉ ቤቶች
የሚከተሉትን የቤት አይነቶች በውጭ ሀገር ዜጋ በባለቤትነት ሊያዙ አይችሉም፦
- በመንግስት ቀጥተኛ ድጎማ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም)።
- ለመንግስት ወይም ለትርፍ ያልተቋቋሙ ህዝባዊ መኖሪያ ቤቶች።
- መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች (NGO) ወይም በመንግስት ድጋፍ የተገነቡ ቤቶች።
- በህብረት ስራ ማህበራት የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች።
እንዲሁም በሽብር፣ በህገወጥ የሰዎች ወይም የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በዕጽ፣ በገንዘብ ማጭበርበር፣ በከባድ ሙስና እና በሳይበር ወንጀል የተጠረጠረ ወይም ጥፋተኛ የተባለ ሰው ቤት መግዛት አይችልም።
ረ) አስተዳደራዊ እርምጃዎች እና የገንዘብ መቀጮዎች
መመሪያውን መጣስ በዶላር የሚቀጣ ከፍተኛ የገንዘብ መቀጮዎችን ያስከትላል፦
- ቤቱን ላልተፈቀደ ወይም ለህገ-ወጥ ዓላማ መጠቀም፦ ከ1,000 እስከ 3,000 ዶላር መቀጮ።
- ያለ ሚኒስቴሩ ፈቃድ ቤት ወይም መሬት ይዞ መገኘት፦ ከ2,000 እስከ 5,000 ዶላር መቀጮ።
- አነስተኛውን የካፒታል መጠን ሳያሟሉ ቤት ገዝቶ መገኘት፦ ከ500 እስከ 2,000 ዶላር መቀጮ።
- ሀሰተኛ ማስረጃ ማቅረብ ወይም ለመጠቀም መሞከር፦ ከ3,000 እስከ 5,000 ዶላር መቀጮ።
- ህገ-ወጥ የቤት ባለቤትነትን የፈቀደ፣ የረዳ ወይም የተባበረ ማንኛውም ሰው፦ ከ30,000 እስከ 50,000 የኢትዮጵያ ብር መቀጮ።
በጥቅሉ ሲገመገም ተዘግቶ ለነበረ የቤት ባለቤትነት መብት ጥሩ የሚባል መመሪያ ነው። ይህ መመሪያ በቀጣይ ለቤት ገዢዎች የሚሰጡ እንደ በአምስት ዓመት በቪዛ የተገደቡ የመኖሪያ መብቶች እየተሻሻሉ ሲሄዱ
- የሪል እስቴት ዘርፉ ለሀገራችን የውጭ ገንዘብ ፍሰት ( FDI) ጥሩ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
- በቤት ግብይት ከሚገኘው ገቢ ባሻገር ግንባታ የሚታየውን የግንባታ ጥራት ደረጃ በማሻሻል በኢንተርናሽናል ደረጃ ተመራጭ የሆኑ ቤቶች ግንባታን ያላምዳል፣
- የግንባታ ቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግርን ያበረታታል
- በአንድ ዓመት ገደብ የተወሰነው የግብይት ጊዜ የግንባታ ፍጥነትን ያሻሽላል
- ተገንብተው ገዢ ላጡ በንጽጽር ቅንጡ ለሚባሉ ቤቶች ገበያውን ያሞቅላቸዋል
- የታክስ ግኝትን ያሳድጋል
- ቤት ገዢዎች በሀገራችን በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ያነሳሳቸዋል


















