በስልጤ ዞን ከወረዳ እስከ ፓርላማ ገዢውን ፓርቲ ወክለው የተመረጡ ተወካዮች፤ በጥቂት ወራት ውስጥ እያንዳንዳቸው 10 ቤት ለህዝብ ካልገነቡ በመጪው ምርጫ የአካባቢው ሰው ድምጽ እንዳይሰጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ። የፌደራል መንግስት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች የግንባታ ዕቅድ፤ እንደ ስልጤ ዞን ባሉ አካባቢዎች በገጠር ኮሪደር ልማት የሚሰሩ ቤቶችን እንደሚያካትትም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ እና የቤት ግንባታ ያስተሳሰሩበትን አስተያየት የሰጡት፤ የዞኑን አመራሮች ጨምሮ ከከፍተኛ የክልል እና የፌደራል ባለስልጣናት ጋር “የገጠር ኮሪደር ስራዎችን” በተመለከተ ትላንት አርብ መስከረም 30፤ 2018 ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በከተሞች ከሚያከናውነው የኮሪደር ልማት በተጨማሪ በገጠርም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት ልክ የዛሬ ዓመት ነበር።
አብይ በገጠር ኮሪደር የመኖሪያ ቤት እና ተያያዥ መሰረተ-ልማት የሚገነቡባቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ አራት ዞኖች ባለፈው ረቡዕ እና ትላንት አርብ ተዘዋውረው ጎብኘተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ፤ ሀላባ፣ ከምባታ፣ ሀዲያ እና ስልጤ ዞኖችን ያዳረሰ ነበር።
አብይ ከዞኑ አስተዳዳሪ ጋር በነበራቸው ንግግር፤ በስልጤ ዞን ብቻ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል እና በፌደራል ምክር ቤቶች “80 የሚጠጉ ተመራጮች” መኖራቸውን እንደተገነዘቡ ጠቅሰው፤ እነዚህ ተወካዮች እያንዳንዳቸው አስር ቤት ቢገነቡ በድምሩ 800 ቤቶች በአካባቢው እንደሚኖሩ አስገንዝበዋል። ተወካዮቹ ቤቶቹን ከመጪው ምርጫ በፊት ገንብተው ማጠናቀቅ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
“እኔ ለስልጤ እህት እና ወንድሞቼ ማስተላለፍ የምፈልገው፤ እነዚህ 80 ሰዎች ቢያንስ አስር፣ አስር ቤት ካልገነቡ በሚቀጥለው ምርጫ አትምረጧቸው። ያልሰራ ሰው መመረጥ የለበትም። ዝም ብሎ እያወራ ምርጫ የሚባል ነገር የለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እነማንን መምረጥ እንደሚገባቸው ጥቆማ ሰጥተዋል።
መንግስታቸው “ከ1.5 ሚሊዮን ያላነሱ ቤቶች” ለመገንባት ማቀዱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህ ማለት አዲስ አበባ ላይ ብቻ የሚገነባ አይደለም። የእናንተን ስራ ጨምሮ ነው። በየቀበሌው፣ በየሰፈሩ የምንሰራቸው ቤቶች ናቸው ተደምረው በሀገር ደረጃ ያንን ውጤት የሚያመጡት” ሲሉም አስገንዝበዋል።
ምንጭ፡ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር


















