የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ25/75 የመንግስት ሠራተኞች የቤቶች ልማት ኘሮጀክት በጋራ ለማልማት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ቤት የሌላቸው የመንግስት ሠራተኞች ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ነው።
የመንግስት ሠራተኛው 25 በመቶ እንዲቆጥብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ 75 በመቶ የባንክ ብድር ይቀርባል ብለዋል።
የብድሩ ጊዜ ለ20 ዓመት የሚከፈል መሆኑን ጠቅሰው፤ 41 ሺህ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። ከፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ መምህራን ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የመንግስት ሠራተኞችን የቤት ችግር መቅረፍ የሚያስችል ነው ብለዋል። ባንኩ 120 ቢሊየን ብር ብድር እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል። የብድር ወለዱ 14 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለ20 ዓመት የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመት የግንባታ ጊዜና አንድ ዓመት ደግሞ የብድር መክፈያ የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷል ብለዋል። ስምምነቱ የመንግስት ሠራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ የቤት ባለቤት የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ አላስፈላጊ ወለድ የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።
ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት


















