በሽያጭ የተላለፉላቸውን የጋራ መኖሪያዎች ውል ፈጽመው የተረከቡ ባለንብረቶች በፍጥነት ወደ ቤቶቻቸው እንዲገቡ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አሳሰበ፡፡
ባለንብረቶቹ በዕጣ የተላለፉላቸው መኖሪያ ቤቶች ባለመግባታቸው እንደ ባለቤት ሆነው ሲያከራዩ የቆዩ መኖራቸውን፣ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በሕገወጥ መንገድ የገቡትን ግለሰቦች እያስወጡ እንደሆነ፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ባለንብረቶቹ ያልገቡባቸው ቤቶች ምን ያህል እንደሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁና ሕገወጥ ድርጊቶች እየተከናወኑባቸው ስለመሆናቸው ግን ጥቆማ በየጊዜው እንደሚቀርብላቸው ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የቤት እጥረት እንዳለ የገለጹት አቶ ሽመልስ፣ በሽያጭ ቤቶቹ የተላለፉላቸው ባለንብረቶች በፍጥነት ካልገቡ ሕጋዊ አሠራሩን በመከተል ቤቶቹ ለሌሎች ተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል፡፡
ባለንብረቶቹ ወደ ቤቶቻቸው ባለመግባታቸው ለጎረቤቶችና ለአካባቢ የፀጥታ ሥጋት መፍጠራቸውን፣ ሕገወጦች ደግሞ እንደ ባለቤት ሆነው ለግለሰቦች እያከራዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ማሳሰቢያውን ከጻፈበት ከመስከረም 20 ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ ባለንብረቶቹ የማይገቡበት ከሆነ፣ የሽያጭ ውሉ እንደሚቋረጥ አቶ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡ እየተፈጸመ ያለው ሕገወጥ ድርጊት ለፀጥታ ሥጋት እንደሆነም አክለዋል፡፡ ውሉ በሕግ አግባብ ከተቋረጠ በኋላ ለሌሎች ቤት ፈላጊዎች እንደሚተላለፉም ጠቁመዋል፡፡
በሽያጭ ያስተላለፋችኋቸው ቤቶች ምን ያህል ናቸው? ተብለው የተጠየቁት አቶ ሽመልስ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በየሳይቶቹ ስላሉ ቁጥራቸውን ምን ያህል እንደሆነ እንደማያስታውሱ፣ ቤቶቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ ግን ለፀጥታ ሥጋት ስለሆኑ ባለቤቶቹ እንዲገቡ ለማድረግ ውሳኔ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

















