እንጂነር ደሳለኝ ከበደ ለሥራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ባቀነኑበት ወቅት የታዛቡትን የቤት ግዢና ሽያጭ ስርዓትን እንደሚከተለው ይገልጻሉ።
(ሙሉ መረጃው ከፌስቡክ ገፃቸው ይተወሰደ ነው።)
“መዝገብህ ባለበት ልብህ በዚያ ይሆናል” እንዲል መጸሃፉ፡፡ትኩረትህ ሁሉ የሚኖረው የኔ የምትለው የምትወደው ነገር ባለበት ቦታ ነው። እኔም በሄድኩበት ሁሉ የሪል እስቴት ነገር ይስበኛል። በልቤ ፍላጎት መሰረት አንዳንዶቹ ጋር ቀጠሮ አስይዤ ሌሎቹ ጋ እንደ መንገደኛ እንግዳ አንኳክቼ ገብቼ ማውጋቴ አልቀረም።
በሄድኩባቸው ዋና ጉዳዬ ያደረግኩት አሰራራቸውን ማወቅና ለእኔም ለወገንም የሚጠቅሙ አሰራሮችም መመልከት ነበር። በዚህ መሰረት የተወሰኑ አሰራሮቻቸውን ከእኛ ጋርና እርስ እርሳቸው አነጻጽሬ ለማቅረብ ሞከርኩ። ሃገሬ ስመለሰ በሰፊው በአካል ለሚመለከታቸው አካላት ከሻይ ቡና ጋር አቀርባለሁ።
በአሜሪካ ቀጠሮ አስይዤ የሄድኩት በሀገር ልጅ በሚመራው በብዙዎች ተመራጭ በሆነው ገላ ሆምስ (Gella Homes) ነበር። በቆይታዬም በገሊላ በኩል ጥሩ አቀባበልና ገለጻ ተደርጎልኛል።
በካናዳ በሪል እስቴት ውስጥ የሚሰሩ የተለያዩ ባለሙያዎችን ቢሮዎቻቸው ሄጄ አናግሬያለሁ። ያው ከተልዕኮ ትምህርት ወደ “አስልቶ አንኳኩቶ ገብቶ ትምህርት” የተሸጋገረ ካሩክለም በሉት ጥሩ ነው። አንኳኩ ይከፈትላችኋል ለእውቀትም ይሰራ ይሆን?
በሁለቱም ሀገራት የሪል እስቴት ግብይት ሂደት ተመሳሳይ የሚባል በተሰመረ መስመር የሚኬድበት ፣ በህግ የሚመራ ፣ የሚመራው አካል ያለ፣ በእውቀትና በስልጡን ባለሙያዎች የሚመራ ፣ የተደራጀ ቋሚ አድራሻና ቢሮ ያላቸው ድርጅቶች የሚመሩት፣ የተለያዩ ባለሙያዎች በትስስር የሚሰሩበት ትልቅ ዘርፍ ነው። የሀገራችን ግብይት ሂደት ከእነሱ አንጻር ሊወዳደር የሚችለው በአንዳንዶች የቢሮ ጥራትና ስፋት ብቻ ይመስለኛል።
በአሜሪካን የውጭ ዜጋ ሆኖ አክቲቭ የሆነ ቪዛ ያለው ሰው እስከ 30% የቤቱን ግምት መክፈል እስከቻለ 70% ድሩስ የሃገሩ ባንኮች ወይም ሌሎች ብድር አቅራቢ ተቋማት ብድር ሰጥተውት ቤት ሊገዛ ይችላል። ብድሩን የሚያመቻቹ የፋይናንስ ባለሙያዎች አሉ። ወድ እምዬ ካናዳ ሲመጣ የቤት ዋጋ በጣም እየተወደደ ስለመጣ ለዜጎቿ ስትል በቪዛ ለሚገቡ ለውጭ ዜጎች ቤት መግዛትን ከልክላለች።
በሁለቱም ሀገራት ቤት መግዛት የፈለገ ገበያ የሚወጣው ብሮከሮች ጋር ነው።
- መጀመሪያ አቅሙን እንዲያሳውቅ ይጠበቅበታል
- ከዚያ ለሚበደረው ያክል ያለውን የክሬዲት ስኮር ያውቃል ( ሀገራት ለመበደር እንደሚያደርጉት ያለ )
- የሪል እስቴት ኤጀንቶች ጋር ሄዶ ፍላጎቱን ያስመዘግባል አብሮ ለመስራት ቃሉን ይሰጣል (ዝም ብሎ ማስለፋት እዚህም እዚያም ማለት የለም)
- በፍላጎቱና በአቅሙ መሰረት የተለያዩ ቤቶች ፎቶ፣ ይዞታውን የሚገልጹ መረጃዎች፣ የሚጠበቁ ማሻሻያዎች፣ የተገነባበት ዓመተ ምህረት፣ ከተገነባበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የቤቱ ታሪክ፣ የመሸጫ ዋጋ፣ ተጠባቂ ታክሶች፣ የኢንሹራንስ ዋጋ፣ ለማከራየት
ከፈለገው ስንት ሊከራይ እንደሚችል፣ በስንት ጊዜ ግብይቱ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ….ወዘተ የሚገልጹ መረጃዎች ይላኩለታል።
- ከተላከው መረጃ የሚመርጣቸውን ቀጠሮ ይዞ በኤጀንቱ አመቻችነት ዞሮ ይጎበኛል።
- ለመረጠው ቤት የመግዣ ዋጋ ያቀርባል ከሻጭ ጋር ወይም ከሻጭ ወኪል ጋር በወኪሉ አማካይነት ተደራድሮ ይስማማል።
- የቤቱ ይዘት በባለሙያዎች ይፈተሻል (Home inspection )
- በስምምነቱ መሰረት ኤጀንቱ (ብሮከሩ) ውል አዘጋጅቶ ለህግ አማካሪ ይልካል ታርሞና ተስተካክሎ ይመለሳል። ወይም የህግ አማካሪው ያዘጋጀዋል።
- ለባንክ ቤቱ የባለሙያ ግምት በቤት ገማቾች ግምት ይሰራለታል ( Appresal)
- ግብይቱ ገዢና ሻጭ ፈርመው ገንዘቡን በባንካቸው ተላልከው ይፈጸማል።
- የኮሚሽኑ ነገር እንደ ብሮከሩ ይለያያል አንዳዶች 5% ከሻጭ ወስደው የገዢ ና የሻጭ ወኪል እኩል ይካፈሉታል ገዢን አያስከፍሉም አንዳንዶች 2.5% ያስከፍላሉ።
የእኛን ግብይት ሁኔታ የበለጠ ለመረዳት የሚፈልግ፦
በማህበራዊ ሚዲያ ከሚንሸራሸሩት አስር ማስታወቂያዎች ሰብስቡና አስሩም ጋር ደውሉ አስር የተለያየ አስራር በአንድ ሀገር ውስጥ ትሰማላችሁ።
ከላይ ከተጠቃቀሱት ባለሙያዎች በተጨማሪ የሪል እስቴት ፎቶ ማንሳትና የሪል እስቴት ሚዲያ ዝግጅቶችም ለብቻቸው የተለዩ ባለሙያዎች አሏቸው።

















