የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ጉባዔ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ ተፈጻሚነት የሚኖረው የንብረት ታክስ አዋጅን በአራት ተቃውሞ በአስር ድምጸ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
የንብረት ታክስ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማስፈን፣ አገልግሎትን በተሻለ ጥራት ለማቅረብና የመሰረተ ልማት ማሻሻያዎችን በቀጣይነት ለመተግበር የሚወጣውን የኢንቨስትመንት ወጪ በንብረት ዋጋ ማደግ ምክንያት በሚጣል ታክስ አማካኝነት ለመሰብሰብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
የፀደቀው አዋጅ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ከተሞች ተፈጻሚነት የሚኖረው ሲሆን÷ ክልሎች አዋጁን መሰረት በማድረግ ከተጨባጭ ሁኔታቸው ጋር በተጣጣመ አኳኋን የየራሳቸውን የንብረት ታክስ ህግ እንዲያወጡ ያስችላልም ተብሏል።
የምክር ቤት አባላት አዋጁ ላይ የፌደራልና የክልል መንግስት ተቋማት እንዲሁም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከንብረት ታክስ ነጻ የተደረጉ ተቋማት መሆናቸውን በማንሳት የሐይማኖት ተቋማት ለምን አልተካተቱበትም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
እንዲሁም ከንብረት ታክስ የሚገኘው ገቢ ለምን አይነት መሰረተ ልማቶች እንደሚውል በግልጽ አዋጁ ላይ እንዳልተቀመጠ ጠቅሰው÷ መብራት፣ ውሃና ሌሎችም የአስተዳደር አገልግሎቶች ላይ የሚስተዋለው ችግርም እንዲስተካከል ጠቁመዋል፡፡
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ÷ በከተሞች በንብረት ታክስ ተብሎ ባይከፈልም ለመሰረተ ልማቶች ህብረተሰቡ እየተመካከረ የሚያዋጣው ገንዘብ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
ለልማት እቅዶች ማስፈጸሚያ ትልቁ የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ነው ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ÷የከተሞች መስፋፋትና አጠቃላይ እድገት ተከትሎ ሰፋፊ የልማት ፍላጎቶች እየመጡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ያሉትን የልማት ፍላጎቶች በመንግስት ወጪ ብቻ መሸፈን እንደማይቻል ገልጸው በቀጣይ ለሚፈለገው ልማት ከተሞች የራሳቸውን የገቢ አቅም ማሳደግ አለባቸው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ከተሞች ከሚሰበስቡት ገቢ ውስጥ የንብረት ታክስ አንዱ መሆኑ፤ አዋጁ የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሁለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ ያቀረበውን የስንብት ውሳኔ አስመልክቶ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ሹመትንም መርምሮ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
ምንጭ፡ የገቢዎች ሚኒስቴር


















