ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአፍሪካ የቤቶች ልማት ምቹ አማራጮችን በሰፊው ለማሳለጥ ከሚሰራው የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ (Big Win Philanthropy) ጋር ውይይት አደረገ።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እና የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ክርስቶፎር ካላቴል ባደረጉት ሰፊ ውይይት በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን፣ ያሉትን ሰፊ እድሎች እንዲሁም አለምአቀፍ የአቅም፣ የጋራንት እና የገበያ አማራጮችን መርምረዋል።
በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያን ሰፊ ህዝብ እና ከፍተኛ የቤት ፍላጎት እንደ ችግር ሳይሆን እንደ መልካም እድል መቀበል እንደሚገባ ተነስቷል።
በዚህም መሰረት በቀጣይ በሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተዋንያንን ያካተቱ ስር ነቀል የቤቶች ልማት ግንባታዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
ሁለቱ አካላት አለም አቀፍ የአቅም፤ የጋራንትና የገበያ አማራጮችን በመጠቀም በሀገሪቱ የቤቶች ልማት ስራዎችን ለማሳለጥ በሚያስችሉ የትብብር እና የአጋርነት ማዕቀፎች ዙሪያ መክረዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያም አሁን ላይ ያሉትን ሰፊ እድሎች በመጠቀም በጋራ ለመስራት እና አጋርነቱን ለማጠናከር ሙሉ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።
ምንጭ:- ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ


















