በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9፣ ከደምበል ወደ መስቀል ፍላወር በሚያመራው መንገድ ላይ በሚገኘው ጋዜቦ አደባባይ አካባቢ ኅዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4፡30 ገደማ በደረሰ የሥራ ላይ አደጋ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተረጋገጠ።
አደጋው የደረሰው ሠራተኞቹ በግንባታ ላይ ባለ አንድ ሕንጻ ላይ የዕለት ሥራቸውን በማከናወን ላይ ሳሉ፣ ቆመውበት የነበረው ርብራብ በድንገት በመፍረሱ ከ12ኛ ፎቅ ላይ በመውደቃቸው ነው። በስፍራው የነበሩ ነዋሪዎችና መንገደኞች በድንገተኛው ክስተት ከፍተኛ ድንጋጤና ሐዘን ውስጥ መውደቃቸው ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና መምሪያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ቶማስ እሸቴ ለኤኤምኤን በሰጡት መግለጫ፣ ሦስቱም ሠራተኞች ከሕንጻው ላይ በመውደቃቸው ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን አረጋግጠዋል።
አያይዘውም የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን የአደጋውን መንስኤና የደረሰውን ጉዳት ዝርዝር ሁኔታ ለማጣራት ምርመራ እያካሄዱ መሆኑን ጠቁመው፣ የምርመራው ውጤት ሲጠናቀቅ ተጨማሪ መረጃዎች ይፋ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።


















