የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማኅበር የቦርድ አባል ዝናቡ ተበጀ (ኢንጂነር) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሲቪል ምሕንድስና፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ እንዲሁም በፕሮጀክት ማኔጅመንት ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በእስራኤል፣ በቤልጂየምና በሆላንድ እንዳገኙም ያስረዳሉ፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ያህል የሪል እስቴት በማቋቋም በቤት ግንባታ፣ በማማከርና በማስተማር ተሰማርተው የቆዩ የምሕንድስና ባለሙያ ናቸው፡፡ ለአሥር ዓመታት ያህል በዩኒቨርሲቲ መምህርነት የቆዩት የምሕንድስና ባለሙያው በዘርፉ የተለያዩ የጥናት መጽሔቶችንም ማሳተማቸውን ይገልጻሉ፡፡
የአፍሪ ኮም ሪል እስቴት፣ አፓርትመንትና ኮንሰልታንሲ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በቅርቡ የተመሠረተው የሪል እስቴት አልሚዎች ማኅበር ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ለመምከር ባዘጋጀው ኮንፍረንስ በቀረበ የመወያያ ጽሑፍ የውይይት ተሳታፊ የነበሩት ዝናቡ (ኢንጂነር)፣ የሪል እስቴት ዘርፉን ቁመና በተመለከተ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡– አፍሪኮም ሪል እስቴት ማነው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– ድርጅታችን በአገሪቱ ካሉ ሪል ስቴቶች ፕሮጀክቶችን በአንድ ዓመት ውስጥ ባለ12 እና 13 ፎቆችን ስትራክቸር ጨርሶና ካርታ አውጥቶ ቤቶች ያስረክባል፡፡ ትልቁ ትኩረታችን ቤት አጠናቆ ማስረከብ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህች አገር የተቸገረችው ቤት አጠናቆ የሚያስረክብ አልሚ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– የሪል እስቴት አልሚዎች ማኅበር ምሥረታን ተከትሎ ከሰሞኑ በተካሄደው ኮንፈረንስ እርስዎ ተወያይ ነበሩ፡፡ በመድረኩ የዘርፉ ሰፋ ያሉ ችግሮች ተነስተው ነበር፡፡ በመሆኑ ዘርፉ ምንድነው የገጠመው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– እንግዲህ እንዳየኸው በዚህ ፕሮግራም ሪል እስቴት አልሚው ብዙ ችግር እየገጠመው መሆኑን አቅርቧል፡፡ ለአብነት አንዳንዱ ጥሩ ያልሆነ ድርጅት ቤት ገንብቶ ለገዥው ስለማያስተላለፍ ሁሉንም ያሰድባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ፖሊሲና ሕግ ሊመለሱ የሚገባቸው የጋራ ችግሮች በመኖራቸው፣ የመንግሥት አካላት ከአልሚው ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት የተካሄደ መድረክ ነው፡፡ በመድረኩ ከተነሱ ሐሳቦች መካከል ለምሳሌ አንዱ አብሮ ማልማትን የተመለከተ ነው፡፡
በመንግሥትና በግሉ ዘርፍና በድርጅትና በግለሰብ መካከል በሚደረግ ትብብር የሚፈጸም የቤት ልማትን የተመለከተ ሐሳብ ተነስቷል፡፡ መንግሥት በ70/30 ፕሮግራም ከተለያዩ ትልልቅ ድርጅቶች ጋር በመዋዋል ቤቶችን ለማልማት እየሠራ ነው፡፡ ሁለተኛው ግን ወሳኝ በሚባሉ አካባቢ ለምሳሌ እንደ ቦሌ ወይም ቂርቆስ አካባቢ የሚገኙ ቦታዎች በይዞታ ባለቤቶች የተያዙ በመሆናቸው፣ እነሱ ለአልሚው መሬት ይሰጡና አልሚው ቤት ገንብቶ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ሲደረግ ባለይዞታዎቹ ከቦታቸው አይፈናቀሉም፣ የመሬቱ ዋጋ ወደ ንብረት ተቀይሮ ሲመነዘር የበለጠ የሚያወጣ ይሆናል፡፡
ስለዚህ በፋይናንስም በማኅበራዊ ሕይወትም ረገድም የተሻለ ጥቅም ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ዓይነት አሠራር አልሚው ከባለይዞታው ጋር ተነጋግሮ እያለማ ቢሆንም፣ ከባለይዞታዎች ጋር ለማልማት መንግሥት እንደ ሐሳብ ይቀበለዋል እንጂ የሕግ ማዕቀፍ የለውም፡፡ ለምሳሌ ውልና ማስረጃ ብትሄድ ሁለት ድርጅቶችን እንጂ ግለሰብን ከድርጅት የሚያፈራርሙበት ሕግ የላቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ባለይዞታዎች ከአልሚዎች ጋር መፈራረም ስለማይችሉ ውልና ማስረጃ በመሄድ መጀመሪያ የሽያጭ ውል በሚል ይዞታው ወደ አልሚው ከዞረ በኋላ፣ ከዚያ ቀጥሎ በመንደር ውል በመዋዋል መሬቱን ስሰጥህ ይህን ያህል ቤት ገንብተህ ትሰጠኛለህ በማለት ትዋዋላለህ፡፡ በዚህ ሒደት ከባለይዞታ ጋር የተዋዋለው አልሚ ‹‹ዱርዬ›› ከሆነ ቤቱን ሊሸጠው ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ባለይዞታዎች ተኝተውም ፀሎት የሚያደርጉት የዚያን ሰውዬ ጤንነትና ደኅነት ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተቃራኒው ደግሞ አልሚው ደግ ከሆነ የሚቸገረው ባለይዞታዎች ብር ስለሌላቸው መጀመሪያ ገንዘብ ይከፍላል፡፡ አሹራ ይከፈልላቸዋል፣ ከዚያ ካርታው ይዞራል፣ ቤቱ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ይህንንም ለማዞር አሹራ ይከፍላል፣ ለተላለፈው ቤት ተጨማሪ እሴት ታክስ ይከፍላል፣ የትርፍ ግብር ይከፍላል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ባለይዞታው ቤቱን እንደሸጠ እንጂ በመሬት እንደተቀያየሩ ተደርጎ የማይወሰድ በመሆኑ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ነገር ሲደማመር ገበያውን ከባድ ያደርገዋል፣ ፈተና ውስጥ ይከተዋል፡፡ ትክክለኛ የሆነ ውል አይፈጸምም፡፡
ስለዚህ መንግሥት ይህን ችግር በመመልከት መሬት ላይ የሚወርድ የሕግ ማዕቀፍ ማበጀት አለበት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መልማት የሚገባቸው ትንንሽ ቦታዎች ወደ ላይ በሚሠሩ ፎቆች ብዙ ቤቶችን መያዝ አለባቸው፡፡ ከተማዋ እየጠበበች የሕዝቡ ብዛትና የቤት ገዥው እየጨመረ በመሆኑ ይህ በባለይዞታና በአልሚው መካከል የሚደረግን ስምምነት በሕግ እንዲገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡– በባለይዞታና በአልሚው መካከል በሚደረግ ስምምነት ቤቱ እየተገነባና ሥራው እየተሠራ ከሆነ መንግሥት እንዴት ሕግ ማበጀት ተሳነው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ የመንግሥት ቢሮክራሲ ነው፡፡ ግንዛቤው አላቸው፣ እኛም ግንዛቤም አስጨብጠናል፣ የተለያዩ ፕሮፖዛሎችን አስገብተናል፡፡ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበናል፣ ሪል እስቴት አልሚዎች በየፊናቸው እየሄዱ ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን ቢሮክራሲው የራሱ የሆነ ሰንሰለት አለው፣ ያንን ሰንሰለት በማሳጠር ወደ መፍትሔ መሄድ መቻል አለበት፡፡ እስካሁን ያገኘናቸው የመንግሥት አካላት ችግሩ እንዳለና መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ይገነዘባሉ፣ ማነቆው ግን አልተፈታም፡፡
ሪፖርተር፡– ይህ ዓይነቱ አሠራር የቤት ችግርን በምን ያህል ይፈታዋል?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– ሦስት ጥቅም አለው፡፡ አንድ ቤተሰብ በ500 ካሬ መሬት ላይ ሁለት ወይም ሦስት ቤት አከራይቶ ሊኖር ይችላል፡፡ እዚህ መሬት ላይ ወደ ላይ ሕንፃ ሲገነባ 50 ወይም 100 ቤቶች ይይዛል፡፡ ይህ የቤት ተደራሽነቱን በስንት እጥፍ እንዳሳደገው ማየት ትችላለህ፡፡ ሁለተኛ ጥቅም እዚህ መሬት ላይ የነበሩ ሰዎችን የኑሮ ደረጃ ያሳድጋል፣ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ያደርጋል፣ ለመንግሥትም የተሻለ ግብር ያስገኛል፡፡ አሠራሩም የመንግሥት ፖሊሲ ይደግፋል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– በሪል እስቴት ዘርፉ ያሉትን የቢሮክራሲና የአሠራር ማነቆዎች ለመፍታት ራሱን ችሎ የሚመራው ተቋም እንዲቋቋም በማኅበሩ ኮንፈረንስ ላይ ተጠይቆ ነበር፡፡ ይህ ምን ማለት ነው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– መንግሥት የራሱ አቅጣጫ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ የሪል እስቴት ዘርፉ በአገራዊ ጠቅላላ ምርቱ ላይ በትልቁ ተፅዕኖ ያለውና እየጨመረ ያለ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ በጣም ብዙ ሰዎች ይሳተፋሉ፡፡ በከፍተኛ መጠን ታክስ ይከፍላሉ፡፡ የቤት ችግርን ለመቅረፍ በሰፊው ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ የግብርና፣ የመስኖና የውኃ ተብሎ ሚኒስቴር እንተቋቋመው ሁሉ የሪል እስቴት ዘርፉን የሚመራ ተቋም ለምን አይቋቋምም የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በአሥር ዓመት ውስጥ 5.5 ሚሊዮን ቤቶች መገንባት አለባቸው ብሏል፡፡
በየዓመቱ ወደ 486 ሺሕ ቤቶች ፍላጎት እያደገ እንደሚሄድ ጥናት አለ፡፡ ይህ ማለት ከከፍተኛ ፍላጎት አንፃር እየተሠራ ያለው በጣም ትንሽ ነው፡፡ ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ቤቶች መሠራት አለባቸው፡፡ ይህ ማለት ዘርፉን የሚከታተለው፣ የተለየ መዋቅርና ብቃት ያለው፣ ጥናቶችን የሚሠራ ቴክኖሎጂ፣ ዘዴዎችንና ሲስተሞችን ማልማት የሚችል ራሱን የቻለ ተቋም ያስፈልጋል፡፡
ስለቴክኖሎጂ ሲወራ ለምሳሌ በቱርክ አንድ ባለ20 ፎቅ ሕንፃ በ20 ቀናት ይጨርሳሉ፡፡ ሌሎች አገሮችም ቢሆን እንደዚህ ይጨርሳሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ወደ አገራችን መምጣት አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ ባለው የቤት ዋጋ ውድነት ምክንያት ከሪል እስቴት መግዛት ሕልም እየሆነ ነው፡፡ የአዲስ አበባ የቤት ዋጋ ኒዮርክና ለንደን ካለው የቤት ዋጋ ጋር በማነፃፀር አዲስ አበባ አልቀመስ አለች እያሉ የሚናገሩ አሉ፡፡ አዲስ አበባን እንዲህ ውድ ከተማ ያደረጋት ምንድነው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– በሁለት ወይም በሦስት ከፍለን እንየው፡፡ ለምሳሌ ውድ የሚባለውን ለቅንጦት የሚሠሩ የሪል እስቴት አልሚ ካምፓኒዎች አሉ፡፡ መግዛት የሚችሉ ይኖራሉ፡፡ አብዛኛው ሪል እስቴት ደግሞ መካከለኛ ገቢ ያለውን ሰው ያማከለ ነው፡፡ ከዚህ ወደ ታች ያለውንና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ ለምሳሌ የመንግሥት ተቀጣሪውን ዓይነት ባገናዘበ መንገድ ራሱን የቻለ አሠራር ተቀርፆ የቤት ፍላጎትን ተደራሽ ማደረግ ያስፈልጋል፡፡ ተመጣጣኝና ተደራሽ የሆነ የቤት ፍላጎት ማለት ለምሳሌ ዓለም አቀፍ ትርጉሙን ብናይ፣ አንድ ተቀጣሪ አንድ-ሦስተኛ ደመወዙን ቆጥቦ በአሥር፣ በ20 ወይም በ30 ዓመት ቤት የመግዛት አቅምን መፍጠር ማለት ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ይህን ለማድረግ የአንድ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ አማካይ አሥር ሺሕ ብር ደርሷል ብለን ብንገትም፣ የዚህ ደመወዝ አንድ-ሦስተኛ ወደ 3,300 ብር ይሆናል፡፡ ይህን ገንዘብ በ20 ዓመት ብታበዛው ወደ 800 ሺሕ ብር መቆጠብ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው በ20 ዓመት በሚቆጥበው ገንዘብ የሚሰጠው ቤት ተመጣጣኝ የሚባል ነው፡፡ እነዚህን ቤቶች ሪል እስቴት አልሚው ይሥራው ከተባለ ልዩ ዕገዛዎች ያስፈልጉታል፡፡
ለምሳሌ በኬንያ ተመጣጣኝ ቤት ለሚሠራ 30 በመቶ ከሆነ የትርፍ ታክስ ይቆረጥበት የነበረው ወደ 15 በመቶ ይቀነስለታል፡፡ መሬት በነፃ ይሰጠዋል፡፡ ብድር ይቀርብለታል፡፡ ግብዓት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ ይፈቀድለታል፡፡ ኬንያም ብቻ ሳይሆን በሌላው ዓለም ጭምር የሚተገበር ነው፡፡ አየህ እኛ አሁን እንደ ሪል እስቴት አልሚ ከምንወስደው የባንክ ብድር ከአሥር በመቶ በላይ ለፋይናንስና (Financial Expense) 20 በመቶ ደግሞ ለመሬት ወጪ ነው የምናውለው፡፡ መሬት በነፃ ቢሰጥህ ከቤቱ ዋጋ 20 በመቶ ይቀነስ ነበር ማለት ነው፡፡ በተጨማሪ በ50 ወይም በ40 ካሬ መሬት ላይ ባለ30 አንድ መኝታ ተመጣጣኝ ቤት በመሥራት በካሬ ሜትር 80,000 ብር ብትሸጥ ዋጋው 2.4 ሚሊዮን ማለት ነው፡፡ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በግማሽ ብትቀንስ ቤቶችን ለማቅረብ የሚቻልበት መንገድ መፍጠር ይቻላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ አልሚዎች አሁን ባለቡት ሁኔታ ተደራሽ ቤት ያቅርቡ ማለት አያስኬድም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም ኮንዶሚኒየም ቤቶች 20/80፣ 10/90 እየተባሉ በድጎማና በልዩ ድጋፍ ነው የተገነቡት፡፡
ስለዚህ በተለያየ መንገድ ድጋፍ ከተደረገ ለምሳሌ ዕቃዎችን በብድርና በጅምላ አምጥቶ በመስጠት፣ መሬት በማቅረብና የፋይናንስ አቅርቦትን በማሟላት መደገፍ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ እኛ ለቤት ሽያጭ ማርኬቲንግ ባለሙያ የምንከፍለው ከሳባት በመቶ በላይ ነው፡፡ ባንክ የሚያበድረን በ21 እና በ22 በመቶ ወለድ ነው፡፡ ይህንን ስትመለከት ወጪን ደማምረህ የምታገኘው ከግብር በፊት ትርፍ ከ20 በመቶ ያነሰ ነው የሚሆነው፡፡
ሪፖርተር፡– ስለትርፍ ሲነሳ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ ወይም በቻይና ያሉ ቤት አልሚዎች ትርፍ ከአምስት እስከ 50 በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ሪል ስቴቶች ደግሞ እስከ 200 ፐርሰንት ድረስ እያተረፉ ናቸው የሚሉ መረጃዎች ይሰማሉ፡፡ እውነታው የት ላይ ነው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– እንግዲህ ከዚህ ቀደም 300 እና 400 በመቶ ታተርፋላችሁ ተብሎም ሲጠየቅ ነበር፡፡ ግን ይህንን ቁጥርን ለመጥራት ደፋር ለሆነ ሰው እንጂ ከእውነታው ጋር የማይገናኝ ነው፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ለግንባታ ብሎ በካሬ ሜትር ያሰፈረው ዋጋ 45,000 ብር ነው፡፡ ነገር ግን ከግንባታው ውጪ የመሬትን ዋጋ ነግሬሃለሁ፡፡ ሌላውን የነገርኩህን ስትጨምር አጠቃላይ ዋጋው እያበጠ ይሄድና የመጨረሻ ዋጋው የናረ ይሆናል፡፡ ወጪዎችን ልዘርዝር ካልክ የመሬት ዝግጅት፣ የዲዛይን ፈቃድ፣ የውኃና ፍሳሽ፣ የአማካሪ፣ የአደጋ፣ የመጠባበቂያ፣ የማርኬቲንግን ጨምሮ በርካታ ዓይነት ናቸው፡፡ ከላይ የጠቀስኩልህን ወጪዎች ስትደምር በአጠቃላይ 90 ሺሕ ብር በካሬ ሜትር ቢሆንና አልሚው በካሬ 110 ሺሕ ብር ቢሸጥ የሚያገኘው ትርፍ ከግብር በፊት 20 በመቶ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የተጣራው ትርፍ ደግሞ አሥራ ምናምን በመቶ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ትርፍ ደግሞ በዓመት ሳይሆን ቤቱ ባለቀበት በሦስት ወይም በአምስት ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ አትራፊ ናቸው፡፡ በጣም ያገኛሉ የሚባለው ከእውነት የራቀ ነው ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ዘርፉ አትራፊ ካልሆነ አዲስ አበባን ያጨናነቋት ሪል ስቴቶች ለምን ዘርፍ ቀይረው አይንቀሳቀሱም?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– ሪል እስቴት በጣም አትራፊ ሆኖ አይደለም፡፡ ይህ ዘርፍ ከሌላው የሚለየው አምራች ኢንዱስትሪ ጋ ልሂድ ብትል ሠርተህ፣ ገንብተህ ከዚያ በኋላ ነው ዕቃ ሸጠህ ገንዘብ የምታገኘው፡፡ ሪል እስቴት ላይ ግን ቅድመ ግንባታ ቤት ትሸጣለህ፣ ከሰዎች በተቀበልከው ብር ነው የምትገነባው፡፡ ስለዚህ ለፋይናንስ ፍሰቱ ቅርብ ስለሆነ ብዙ ካምፓኒዎች ወደ እዚህ ዘርፍ ይገባሉ፡፡ ሁለተኛው ከተማ ውስጥ የምትሠራው በመሆኑ ለደኅንነት አሥጊ አይደለም ብለው ይገቡበታል፡፡ በጣም ጥቂቶች ደግሞ በዘርፉ ልምድና ዕውቀት ኖሯቸው ፍቅርም ኖሯቸው እዚያ ላይ የሚንቀሳቀሱና የሚሠሩ አሉ፡፡ በአብዛኛው ትርፍ አለው ብሎ ዘው ብሎ የገባውን ግን ስታይ እየከሰረ እየወጣ ነው፡፡ የተመዘገቡና መሬት ላይ ያሉ ሪል ስቴቶችን ስታይ በጣም የተለያዩ የቁጥር ልዩነቶች ናቸው ያሉት፡፡
በሪል እስቴት ዘርፍ ወደ 25 ዓመታት ቆይቼያለሁ፡፡ አሁን በሪል እስቴት ዘርፍ ተሰማርተህ ስትሠራ የአምስት ዓመት ግንባታ ካለህና ዛሬ ቤቱን ቅድሚያ ሸጠህ ከጨረስክ አለቀልህ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋጋ ንረት በጣም ከባድ ነው፡፡ ዛሬ የምትሻሻጥበት ብር የዛሬ ሁለትና ሦስት ዓመት በኋላ ከሚኖረው ዋጋ ጋር የተለያየ ነው፡፡ እኛ እየሠራን ያለነው ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ ዓመት የምንጨርሰውን የቤት ፕሮጀክት የመሥራት ስትራቴጂ በመከተል ነው፡፡ ምክንያቱም የብረትን ዋጋ ብትመለከት በሁለት ዓመት ውስጥ ከ100 ብር ወደ 170 ብር፣ ሴራሚክ ከ800 ወደ 1,500 ብር ገብቷል፡፡ ሲሚንቶም ቀነሰ ይባላል እንጂ አሁንም መውረድ አለበት፡፡ በአጠቃላይ የግብዓቶች ዋጋ በሁለት ዓመት ውስጥ ከ70 እስከ 80 በመቶ አሻቅቧል፡፡ ይህ ማለት የዛሬ ሁለት ዓመት ቤት የሸጠ አልሚ ጉድ ሆነ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– አንድ የሪል እስቴት አልሚ አንድ ቤት በሦስት ዓመት በአሥር ሚሊዮን አጠቃላይ ዋጋ ለመጨረስ ከተስማማ በኋላ በሦስተኛው ዓመት ቤቱን አያደርስም፣ የቤቱ ዋጋም በጣም ጨምሯል፡፡ በዚህ ምክንያት ከገዥዎች ጋር ለሚፈጠር አለመግባባት ማነው ተጠያቂው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– ይህን ጉዳይ መጀመሪያ የሚፈታው ኮንትራቱ ነው፡፡ በኮንትራቱ መሠረት በአንድ ዓመት እጨርሳለሁ ብሎ ውል ከገባ በኋላ በእሱ ክፍተት ሦስት ዓመት ከሆነ የፈጀው አልሚው ኃላፊነቱን ይወስዳል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በአንድ ዓመት እጨርሳለሁ ብሎ ከዋጋ ንረትና ከዶላር ጋር የሚኖረው ምንዛሪ ካሽቆለቆለና አልሚው ሥራውን እየሠራ ከሆነ በመተዛዘን ቁጭ ብሎ መመካከር ያስፈልጋል፡፡ የተገዛው ቤትም ገበያው ውስጥ ዋጋው ስለሚጨምር ይህም መታሰብ አለበት፡፡
ትልቁ ጉዳይ መሆን የሚገባው አልሚው በዋጋው ላይ ያልተገባ ድርጊት አድርጓል ወይ? ኮንትራቱ ምን ይላል? የዋጋ ንረት አለው ወይስ የለውም? የሚለው መታየት አለት፡፡ ጉዳዩ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ እኛ ሪል እስቴት ላይ የምንመክረው የአጭር ጊዜ በተለይም ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ሊያልቁ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን እንዲያዙ ነው፡፡ አሁን ባለው ገበያ የሚፈጠሩ ያልተጠበቀ ክስተቶች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ የአልሚዎች ማኅበርም የተመሠረተበት ዓላማ እንደዚህ ዓይነት አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ችግሩ ይቀርብለታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደ ማኅበሩ መጥተው መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡ የሚገርምህ በእንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ ገብተውና ብዙ አለመግባባቶች ተጠራቅሞባቸው የነበሩ ብዙ ሪል ስቴቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ማኅበሩ ደንብ እያዘጋጀ ነው፡፡
በቀጣይ የሚሠራበት ይሆናል፡፡ ሦስት ዓይነት የሪል እስቴት ኩባንያዎች አሉ፡፡ አንደኛው ሥርዓት ያለው (Disciplined) የሆነ፣ የፕሮጀክትና የፋይናንስ አመራሩ ንፁህና ጥሩ የሆነ፣ የሚመጣውን ገንዘብ የታቀደው ፕሮጀክት ላይ የሚያውል፣ ጊዜውን ጠብቆ የሚሠራና የሚበቃውን የሚጎርስ ድርጅት አለ፡፡ ይህ ስኬታማ ድርጅት ነው፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ድርጅት የረዥም ጊዜ ፕሮጀክት የያዘ፣ ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ክስተቶችን ለመገመት የሚቸገር፣ ሊፈጠርና ሊገጥም የሚችል ሁኔታን ለመገመት የሚቸገር ዓይነት ነው፡፡ ሦስተኛው ዓይነት ድርጅት ደግሞ በፍፁም ቤት ገንብቶ ማስረከብ ላይ የሌለ፣ የሚያወራው የሚተገብረው የማይገናኝ፣ ብሩን ሰብስቦ የሚጠፋ፣ ሌላ ድርጅት የሚከፍትና በሰው ገንዘብ V8 መኪና የሚያገላብጥ ይኖራል፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው ገና ‹‹አያያዙን ዓይቶ ጭብጦውን ቀማው›› እንደሚባለው ወዳቂ ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ዓይነት ድርጅት ቤት ገንብቶ ያስተላልፋል፡፡
በብዛት ጭቅጭቅ ያለባቸው ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ቤቶች ናቸው፡፡ ቁጥራቸው አነስተኛ ነው፡፡ ሁለተኞቹ ግን ዓላማቸው ለአራትና ለአምስት ዓመት የሚቆዩ ፕሮጀክቶችን መያዝ ነው፡፡ ምክንያት ከቤት ገዥዎች ጋር ማውራት አለባቸው፣ ከሕግና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በተገናዘበ መንገድ ተቀምጠው መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– በቅርቡ የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ባለቤት የሚሆኑበት የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶ ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡ አንዱ የረቂቁ ዓላማ የአገር ውስጥ አልሚዎችን ማበረታታት ነው ይላል፡፡ ይህ ረቂቅ ሕግ በአልሚዎች ዘንድ እንዴት ታይቷል?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– ኢትዮጵያ የውጭ ሪል ስቴቶችን ለመቀበል ዝግ የነበረውን በር ገርበብ አድርጋ እየጠበቀች ነው፡፡ ሪል ስቴቶች መምጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ቀድመው አይሸጡም፣ ገንብተው ነው የሚሸጡት፡፡ በሕግ ማዕቀፍ እንደተቀመጠው ይህ ተደራሽነትን ያሰፋዋል፡፡ ጥሩ ድርጅቶች ከሆኑ የዕውቀት ሽግግር ያደርጋሉ፣ ቴክኖሎጂ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕንፃ አጨራረስ ባለሙያ መሐንዲስ የለንም፡፡ በዚህ ረገድ የውጭ አገር ባለሙያዎችን ልምድ የመቅሰም ባህሉን ሊያሳድግ ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ አገራችን የገቡ የውጭ ሪል ስቴቶችን ቀረብ ብለን ያለባቸው ችግር ምንድነው ብለን መጠየቅና መነጋገር ባያስፈልግም፣ ነገር ግን ቤት በወቅቱ እያስረከቡ አይደሉም፡፡
ስም መጥቀስ ቢያስፈልግም የእነዚህን ድርጅቶች ችግር መጀመሪያ መፈተሽ ያለበት ቢሆንም፣ ጊዜና ዋጋውን ጠብቀው እየጨረሱ አይደሉም፡፡ ስለዚህ አሁን ሕጉን ከማውጣት በፊት ከእነዚህ የውጭ ድርጅቶች ትምህርት ቀስመናል ወይ የሚለው መፈተሽ መቻል አለበት፡፡ የውጭ አገር ገንቢን ስናስገባ ጥቅም ቢኖረውም ጥቅሙ በትምህርተ ጥቅስ ሆኖ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ለኮንስትራክሽን ግንባታ የምትጠቀሙት ግብዓት ከውጭ አገር የሚመጣው ከአጠቃላይ ግብዓቱ ምን ያህል የሚሆነው ነው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– የአንድ ፕሮጀክት 70 እና 80 በመቶ የሚሆነው የግብዓት ወጪ ነው፡፡ ከዚህ ግብዓት አብዛኛው የሚባለው ከውጭ የሚመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብረት ፋብሪካ አለ፡፡ ይህ ፋብሪካ ግን የብረት ቁርጥራጭ አምጥቶ የሚያቀልጥ እንጂ፣ የብረት ቅይጥ ከመሬት የሚያወጣ አንድ ፋብሪካ የለም፡፡ ለምሳሌ ሰቆጣ መሬቱ ውስጥ ብረት አለ፣ የሚያወጣ ፋብሪካ የለም፡፡ ያሉት ፋብሪካዎችም ሥራቸው ቁርጥራጭ ማቅለጥ ነው፡፡ ነገር ግን የአንድ ፕሮጀክት 20 በመቶ ወጪው ብረት ነው፡፡ ስለዚህ አብዛኛው ግብዓት ለምሳሌ ሊፍት፣ ትራንስፎርመር፣ አልሙኒየም፣ ብረት፣ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችና ሌሎችንም ጨምሮ ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡– ከውጭ የሚመጡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ ቀረጥ እንዲቀንስ ጥያቄ እያቀረባችሁ ነው?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– አዎ፣ ለሪል እስቴት ዘርፉ ቀረጥ ቢስተካከል የቤት ዋጋን በጣም ይቀንሰዋል፡፡ መንግሥት አሁን ያንን ሙሉ ለሙሉ ላያደርግ ይችላል፡፡ ቢያንስ ግን በአጭር ጊዜ ፕሮጀክት ጨርሶ ለሚያጠናቅቅ በቅናሸ ዋጋ ቤት ለሚያቀርብ ተብሎ ግብር መቀነስ ይቻላል፡፡ አረንጓዴ ልማትን የሚያበረታታ ፕሮጀክትና የዝናብ ውኃን እንደገና በድጋሚ ለጥቅም የሚያውሉ ፕሮጀክቶችን ሊያበረታታ ይችላል፡፡ ሌሎች አገሮች ይህን ያደርጋሉ፣ የታክስ ክሬዲት በሚል ይደግፏቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የመሬት እጥረት እንደ ችግር ሊነሳ ይችላል?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– በአዲስ አበባ ሦስት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛው ባዶ መሬቶች አሉ፡፡ ሁለተኛው በተሻለ የሕንፃ ግንባታ ሊተኩ የሚችሉ አካባቢዎች አሉ፡፡ አብረህ የምታለማቸው ዓይነት ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ሊሰፉ የሚችሉ ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጫካ ፕሮጀክት ዓይነት ይዞታዎች እየገቡ ያሉ አሉ፡፡ በእነዚህ ቦታዎች በደንብ ቤት ለመገንባት በሚያስችል መንገድ በሥነ ሥርዓት ከተመራ መሬቱ አያንስም፡፡ እኔን የሚያስፈራኝ የመሬቱ ጉዳይ ሳይሆን ያለው የመሠረት ልማት ቁመና ሊገነባ የሚችልን ቤት ለማስተናገድ አቅም አለው ወይ የሚለው ነው፡፡ የፍሳሽ መስመሮች፣ መንገዶችና የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ይህን መሸከም መቻላቸው መረጋገጥ አለበት፡፡
ለምሳሌ አሥር ሺሕ ቤቶች ሠርተህ ቀጥሎ ያለው፣ አስፋልት አንድ በር ብቻ ከሆነ ያለው በየሰከንዱ በዚህ መንገድ አንድ መኪና ከግቢው ቢወጣ አሥር ሺሕ መኪና ከጊቢው ለመውጣት 3፡00 ሰዓት ይፈጃል ማለት ነው፡፡ 24 ቀበሌ ብትሄድ 40/60 ቤቶች ተሠርው ካለቁ በኋላ ሽንት ቤቱን መልቀቂያ በመጥፋቱ ወንዝ ወስደው ዳሩ ላይ ትንሽ ማጣሪያ ተሠርቶ ወደ ወንዙ ነው የገባው፡፡ ገርጂ ያሉ 40/60 ቤቶችን ስታይ የቤቱ ፍሳሽ እየተንደረደረ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ያለ ወንዝ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ መንግሥት ወንዙ ዳር ላይ ማጣሪያ ገንብቶ ነው የለቀቀው፡፡ ይህ የተፈጠረው በውልና በሥርዓት ያልታሰበበት ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሊፈታ የሚችለውና እኛም ፕሮፖዛል ጽፈን ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት ያስገነባው መሬት አልሚና ቤት አልሚ መለየት አለባቸው የሚል ነው፡፡ በሌላ አገር አልሚው መሬት ይቀይሳል፣ ያርሳል፣ ይደለድላል፣ ያስተካክላል፣ ሽንት ቤቱ እዚህ ላይ ይሠራ ይላል፡፡ የመንገዶችን መስመር ቀይሶ የሆነ ያህል መሬት ላይ የሆነ ያህል ቤት ለመገንባት እንዲያገለግል አድርጎ ያዘጋጃል፡፡ የሪል እስቴት አልሚው በተዘጋጀው መሬት ቤቱን ይገነባል፡፡
ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት አልሚ የለም?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– አዎ፣ መሬት አልሚ የለም፡፡ መንግሥት በትልቁ ማሰብ ያለበት መሬት አልሚና መካከለኛ አቅም ያላቸውን ቤት አልሚዎች ነወ፡፡ መንግሥት አሁን እያየ ያለው ትልልቆችን ሪል ስቴቶች ነው፡፡ ትንንሾቹን በጋራ መጥታችሁ አልሙ ይላል፡፡ ትንንሾቹ በጋራ መጥተው ያልሙ ሲባል ደግሞ አይጣጣሙም፡፡
ሪፖርተር፡– ያልተገነባ አንሸጥም የሚሉ አልሚዎች አንድም ተገንብቶ ጥራት የሌለውና መሠረተ ልማት ያልተሟላለት፣ ወይም በጊዜው በማያጠናቅቁ አልሚዎች ምክንያት ደንበኞች በተደጋጋሚ ሲያማርሩ የሚሰማባቸው ድርጅቶች አሉ፡፡ ምንድነው ችግሩ?
ዝናቡ (ኢንጂነር)፡– በአገር ደረጃ ትልቁ ችግራችን የምንውጠውን አይደለም የምንጎርሰው፡፡ አብዛኛው ድርጅት የምትለው ሳያስበው መስገብገብ ውስጥ ይገባል፣ የያዘውን ሳይጨርስ ሌላ ያምረዋል፣ የሚሠራውን አይደለም የሚኖረው (Walk the Talk) እንደሚባለው፡፡ የምታወራውን መሄድ መቻል አለብህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ግማሹ አስቦበት፣ ግማሹ ሳያስብበት ወደ ወንበዴነት እየተቀየረ ነው፡፡ በሦስት ዓመት አስረክባለሁ ብለህ 15 ዓመት ከቆየህ ቤት ገዥዎች በአንተ ምክንያት የደም ግፊት ተይዘዋል፣ ትዳር ይፈርሳል፣ ራሱን የሚያጠፋ ይኖራል፡፡ ንብረቱን ሸጦ አንተን አምኖ ቤት የገዛ ይኖራል፡፡ ይህ ማለት አልሚው የደሃ ዕንባ እጁ ላይ አለበት፡፡ በተስማማው ጊዜ ጨርሶ የሪል እስቴት አልሚው ቤቱን ካላስረከበ ያ መለካት ያለበት ወደደም ጠላም የደሃ ዕንባ እጁ ላይ እንዳለበት ነው፡፡ ያ ሰው አውቆ ነው ሳያውቅ የሚለው ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ ነገር ግን የዚያ ሰው ዕንባ እጁ ላይ አለበት፡፡ ይህ ደሞ እጁ ላይ ያለበት ሰው እንዴት መስጊድ ወይም ቤተ ክርስቲያን ሊሄድ ይችላል? እንዴት አስራት በኩራት ይሰጣል? እናም እንደ አገር ትልቁ ፈተናችን መጥነን አንጎርስም፡፡ በዚህ ምክንያት እኛም አስከፊ እንሆናለን፣ ለተመልካችም እንቀፋለን፡፡ ስለዚህ አንድ ድርጅት ሥራ ከመጀመሩ በፊት መጀመሪያ አቅሙን ማየት መቻል አለበት፡፡ ገንዘቡን ከዚያ መሬቱን፣ አሸዋ፣ ብረት፣ አልሙኒየምና ሲሚንቶውን፣ ይህን ሥራ የሚያሠራ የሰው ኃይል አለ ወይ የሚለውን በሚገባ ማጥናት አለበት፡፡ የቆመበትን ማረጋገጥ መቻል አለበት፡፡ ምክንያቱም የቆምን ቢመስልም እየተንገዳገድን ሊሆን ይችላል፡፡ ሰው መክሊቱን መፈለግ መቻል አለበት፡፡ ትርፋማ ነው ስለተባልን ብቻ መሮጥ የለብንም፡፡
ጃፓኖች ‹‹የምትወደውን ሥራ›› የሚል ኢኪጋይ (Ikigai) የሚል አባባል አላቸው፡፡ አንድ ሰው የሚሠራውን ሲያስብ ከአልጋው ዘሎ መውጣት አለበት፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ አራት ነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡ እነሱም የምታፈቅረውን ሥራ፣ የምታውቀውን ሥራ፣ ገበያው የሚፈልገውን ሥራና ሊከፈልህ የሚችለውን ሥራ፣ ያን ከሠራህ አትወድቅም ይላሉ፡፡ ይህ ማለት አንድ ሰው ወይም ድርጅት የሚያውቀውን ከሠራ ወደ ሌላ ቀቢፀ ተስፋ አይገባም፡፡ የሚያፈቅረውን ከሠራ የሆነ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ይጨምራል፡፡ ጥሩ ውጤት ያመጣል ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን በጣም እውነተኛና ሀቀኛ የሆኑ ሪል እስቴት አልሚዎች በዋጋ ምክንያት፣ በፋይናንስ እጥረት፣ ገዥው ገንዘቡን በወቅቱ ባለመክፈሉና በመሰል ችግሮች በዕቅዳቸው ልክ የማይሄዱ አሉ፡፡ እነዚህ አልሚዎች መደገፍና መደመጥ አለባቸው፡፡ ገዥውም ማወቅ ያለበት የሚፈልገውን ቤት ለማግኘት በወቅቱ መክፈልና ቤቱን መጠየቅ ነው፡፡
ምንጭ፡ ethiopianreporter


















