በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎችና በግል አልሚዎች መካከል የመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት ትግበራን በጋራ ለማሳካትና ለህብረተሰቡ የመጠለያ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ይበልጥ ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት የተወከሉ ባለሙያ በተገኙበት በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት እና በጊፍት ሪል እስቴት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መካከል የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በጋራ ለመገንባት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ በተፈረመበት ወቅት እንደተጠቆመው የመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት ትግበራ ህብረተሰቡ በየጊዜው ለሚያነሳቸው የመጠለያ ጥያቄዎች የተሻለ ምላሽ በመስጠት የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል የጎላ ድርሻ አለው፡፡

በዚሁ መሰረት ጊፍት ሪል እስቴት በመጀመሪያው ዙር 3 ሺህ 540 የመኖሪያ ቤቶችን፣ 460 ለሱቅ፣ ለትምህርት ቤትና ለሌሎቸ አገልግሎቶች የሚውሉ ሁለገብ ቤቶችን በመሃል አዲስ አበባ ለገሃር አካባቢ የሚገነባ ይሆናል፡፡
ጊፍት ሪል እስቴት በባላገሩ ምርጥ አንደኛ ለሚወጣው የሶስት ሚልዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ግንባታው በሶስት ዓመታት የሚጠናቀቅ ነው የሚሆነው፡፡ የጊፍት ሪል እስቴት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገ/የሱስ ኢጋታ ጊፍት ሪል እስቴት በመንግሥትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ 4 ሺህ ቤቶች በላቀ ጥራት ለመገንባት ዝግጅት ማጠናቀቁን በስምምነቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ በሚደረጉ ስምምነቶች ጊፍት ሪል እስቴት ተጨማሪ 8 ሺህ የሚደርሱ ቤቶችን ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም አቶ ገ/የሱስ አስረድተዋል፡፡

መንግስት የተለያዩ የቤት ግንባታ ሞዳሊቲዎችን በመቅረጽ ወደ ሥራ በገባው መሠረት በይፋ የተጀመረው የመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት ትግበራ የታቀደለትን ዓላማ እንዲያሳካ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና መላው ህብረተሰብ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ጠንክረው መሥራትና ይበልጥ ተቀናጅተው በጋራ መረባረብ እንደሚጠበቅባቸውም በሥነ ስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቀደም ሲልም ከተለያዩ የግል አልሚዎች ጋር በመንግስትና የግል አጋርነት ፕሮጀክት ትግበራ አማካኝነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በጋራ በመገንባት የመጠለያ ጥያቄን በተሻለ አግባብ ለመመለስ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል፡፡


















